ኢትዮጵያ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመከላከል የምታደርገውን ትግል አፍሪካውያን ሊቀላቀሉት ይገባል

59

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የውጭ ጣልቃ ገብነትን እና የእጅ አዙር ቅኝ-ግዛትን ለመከላከል የምታደርገውን ትግል አፍሪካውያን ሊቀላቀሉት እንደሚገባ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ተናገሩ።

ኢትዮጵያ በረዥም ዘመን ታሪኳ ነጻነቷን አስከብራ የኖረች አገር ናት፡፡

ኢትዮጵያውያን የራሳቸው ነጻነት ብቻ ሳያኩራራቸው ለአፍሪካ ብሎም ለጥቁር ህዝቦች ነጻነት በግንባር ቀደምትነት ታግለዋል፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረትም የመሪነት ሚና ተጫውተዋል፡፡

አሁን ላይ አንዳንድ የምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እየተፈታተኑ ይገኛሉ፡፡

እነዚህ አገራት አሸባሪው ህወሃትን በመደገፍ ጭምር በኢትዮጵያ ህልውና ላይ አደጋ የጋረጡ ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያንም በአንድነት ቆመው ለአገራቸው ነጻነት እየታገሉ ይገኛሉ፡፡

ፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያ አማን ኡመር እንደሚሉት አንዳንድ የምዕራባውያን አገራት አፍሪካውያን በሁሉም መስኮች ራሳቸውን እንዳይችሉ ሲሰሩ ይሰተዋላል፡፡

በተለይ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂ መስኮች አፍሪካ የምእራባውያን ጥገኛ እንድትሆን በብርቱ እንደሚሰሩ ነው የሚናገሩት፡፡

በዚህም ኢትዮጵያውያን የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት የሚሹ የውጭ ሃይሎችን ለመመከት ግንባር ቀደም ተጋድሎ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ አፍሪካውያን የኢትዮጵያን ትግል ሊቀላቀሉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

አፍሪካውያን አንድነታቸውን በማጠናከር የምዕራባውያን ጫና መመከት አለባቸው ነው ያሉት፡፡

አፍሪካውያን የውስጥ ችግራቸውን በራሳቸው አቅም መፍታት እንደሚችሉ በተግባር ማሳየት፣ የራሳቸውን ምርት የመጠቀም እንዲሁም የእርስ በርስ ትስስርን ማዳበር እንደሚጠበቅባቸውም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ምእራባውያን የአፍሪካን ሃብትና እውቀት ለመቀራመትና የእጅ አዙር እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባም ነው ያስረዱት፡፡

በኢትዮጵያ እያደረጉት ያለው ሁለንተናዊ ጫና ደግሞ ለዚሁ ማሳያ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል፡፡

የአለማቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ባለሙያው ረቡማ ደጀኔ  በበኩላቸው ምእራባውያን በአፍሪካ ሀገራት ላይ የሚያደርጉት ጫና የራሳቸውን ጥቅም ከመፈለግ የሚመነጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ ጎን በመሰለፍ በሁሉም መስከ ነጻ የሆነች አፍሪካን መገንባት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም