የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ዋንኛው የዘርፉ ትኩረት ነው

65

ጎባ ፤ህዳር 11/2014 ዓ.ም (ኢዜአ) ብቁ የጤና ባለሙያዎችን በጥራትና ብዛት በማፍራት የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ በዋናነት ከሚሰራባቸው ጉዳዮች ዋንኛው የዘርፉ ትኩረት መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል በተለያዩ የጤና መስኮች በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን 229 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል፡፡

በምርቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ እንደተናገሩት፤ ብቁ የጤና ባለሙያዎችን በጥራትና ብዛት በማፍራት የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ተቋማቸው በዋናነት ከሚሰራባቸው ጉዳዮች ዋነኛው ነው፡፡

ሚኒስቴሩ በተለይ በአገሪቱ የሚታየውን የሐኪም-ታካሚ ጥምረትን ለማቀራረብ  ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ  መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን ለማህበረሰቡ ለማዳረስ  እያደረገ ያለው ጥረት እንደሚያደንቁና አገልግሎቱ ይበልጥ እንዲጠናከር ተቋማቸው እንደሚደግፍ አስታውቀዋል፡፡

የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር  ጀይላን ቃሲም በበኩላቸው፤ ተመራቂዎቹ  በተቋሙ ከአራት እስከ ሰባት ዓመት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተው ያጠናቀቁ መሆናቸውን ገልጸዋል ፡፡

ህክምና፣ አዋላጅ ነርስነት፣ የላብራቶሪ ቴክኒሻንና ፋርማሲ ተመራቂዎቹ ከተከታተሉት የሙያ ዘርፎች መካከል አንደሚገኙበት ጠቅሰው፤ ከአጠቃላይ ተመራቂዎች 86ቱ ሴቶች እንደሆኑ አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው በጤናና ሌሎች የተለያዩ የትኩረት መስኮች ተማሪዎችን ተቀብሎ ከማስተማር በተጓዳኝ በስሩ በሚገኘው የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ለህሙማን የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶክተር በዛብህ ወንድሙ ናቸው።

በተለይ በጤናው ዘርፍ የሚሰለጥኑ ተማሪዎች በአካባቢው ብሎም በሀገሪቱ የሚታየውን የህክምና ባለሙያዎች እጥረትን ለማቃለል ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢው ማህበረሰብ እየሰጠ የሚገኘውን የጤና አገልግሎት ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ በሪፈራል ሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ ባለ 8 ወለል ህንፃ እያስገነባ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ከዕለቱ ተመራቂዎች መካከል በአዋላጅ ነርስነት 3 ነጥብ 99 በማምጣት የተመረቀችው ተማሪ በረከት ይልማ በሰጠችው አስተያየት "በተማርኩት ሙያ የእናቶችና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ ለሚደረገው ጥረት ሙያዊ ግዴታዬን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ" ብላለች፡፡

"የተመረቅንበት ወቅት ሀገራችን የጤና ባለሙያዎችን በከፍተኛ ሁኔታ በምትፈልግበት ወቅት በመሆኑ የዜግነትና የሙያ ግዴታዬን ለመወጣት ቁርጠኛ ነኝ" ያለው ደግሞ በሜዲካል ላብራቶሪ ሙያ 4 ነጥብ በማምጣት የተመረቀው ሙሉጌታ ጫሊ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም