በአርሲ ዞን 20 የአሸባሪው ሸኔ አባላት እጃቸውን በሰላም ሰጡ

94

አዳማ፣ ህዳር 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአርሲ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች 20 የአሸባሪው ሸኔ አባላት ለመንግሥትና አባገዳዎች በሰላም እጅ መስጠታቸውን የዞኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ኮሚቴ ሰብሳቢና የዞኑ ዋና አስተዳደሪ አስታወቁ።

በሙኔሳ ወረዳ በተካሄደው ሰላም ኮንፍረንስ ላይ አባገዳዎች በአሸባሪው ሸኔ ላይ የውግዘት ውሳኔ አሳልፈዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የአርሲ ዞን ዋና አስተዳደር አቶ ሙሳ ፎሮ እንደገለጹት፤  በወረዳው ሀገር ለማፍረስ ከተሰለፉ ጠላቶች  ጋር  መሰለፍን ያልፈቀዱ 20 የሸኔ አባላት እጃቸውን በሰላም ሰጥተዋል።

በተሳሳተ አመለካከት የሽብር ቡድኑን ተቀላቅለው ሲንቀሳቀሱ ቆይተው የአባገዳዎችን የውግዘት ውሳኔና ጥሪ ተቀብለው እጅ ሊሰጡ እንደቻሉ ገልጸዋል።

የአርሲ አባገዳዎች 'ልጆቻችን ከባንዳ ጋር አይወግኑም፣ ሀገር አያፈርሱም፣ መክረን ገፅፀን እንመልሳለን' ብለው ቃል በገቡት መሰረት አባላቱ  ከጥፋት መንገድ በመለለስ እጃቸውን በሰላም መስጠታቸውን ተናግረዋል።

በሀሰት ፕሮፓጋንዳ ተታለው ጫካ ገብተው የነበሩት እነዚህ የአሸባሪው ሸኔ ቡድን አባላት ሰላማዊ መንገድ መምረጣቸውን ገልጸዋል።

አባገዳዎችና ማህበረሰቡ ባደረጉት የተቀናጀ ዘመቻ ቀደም ሲልም በርካታ የአሸባሪው ሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አስታውቀዋል።

የሙኔሳ ወረዳ አስተዳደሪ አቶ አማን ሻቁሮ በበኩላቸው፤ በወረዳው  ብቻ አባገዳዎች ባደረጉት ጥሪ ስድስት የሸኔ አባላት በሰላም እጅ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

አባገዳዎች ኃላፊነት ወስደው ባደረጉት የአንድ ሳምንት ዘመቻ እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ መደረጉን አስረድተዋል።

አሁንም የተቀሩት እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ  የአባገዳዎች፣ የአባቶችና የእናቶች ጥሪ  መቀጠሉን አመልክተዋል።

ሸኔ ባለፉት 27 ዓመታት የኦሮሞን ህዝብ ሲያሰቃይ ከነበረው አሸባሪው ህወሓት ጋር ሀገር ለማፍረስ መሰለፉን  አባገዳዎቹ በማውገዝ በሸኔ ስም ጫካ የገቡት የኦሮሞ ህዝብ ጠላት ናቸው በማለት ፈርጀዋል።

የአባገዳዎችን ውሳኔ ያልተቀበሉ፣ የእናትና አባቶቻችን ጥሪ አንቀበልም ያሉ የሸኔ አባላት  የኦሮሞ ሕዝብና የሀገር ጠላት ናቸው የሚል አቋም ይዘው የውግዘት ውሳኔ አስተላልፈዋል።

የአርሲ ሄበን ሸነን አባገዳ ዋቆ ሳቲ ኦብሳ፤  ከአሸባሪዎቹ ሸኔና ህወሃት ጋር ያበረ ማንኛውም አካል የህዝብና የሀገር ጠላት መሆኑን ፈርጀን ውሳኔ አሳልፈናል ብለዋል ።

የኔም ልጅ ቢሆን ከሀገር በተቃራኒ የቆመ እንደሆነ  ጠላት ነው፣ ቢሞት  አልቀብረውም፣ ለቅሶ አልቀመጥም የሚል ውሳኔ ማሳለፋቸውን ነው ያስታወቁት።

ይህን ውሳኔ ወደ ጎን በመተው ጫካ ከገቡት ጠላት ጋር ያበረ፣ ለእሱ ብሎ ለቅሶ የተቀመጠ ከጎሳ የሚገለል ከመሆኑም ባለፈ ከማህበራዊ ትስስር ሁሉ እንደሚታገድ  አስታውቀዋል።

በዚህም  በግንዛቤ ማነስ ሳቢያ በሽብር ቡድኑን በተሳሳተ አካሄድ ጫካ ያሉት ቀሪ  ወጣቶች የአባ ገዳዎች፣ የእናትና የአባቶቻችን ጥሪ ተቀብለው ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ጥሪ በድጋሚ አቅርበዋል።

ጥሪውን ተቀብለው በሰላም ወደ ማህበረሰባቸው ለሚመለሱት ምህረት እንደሚደረግላቸውም አረጋግጠዋል።

እጃቸውን ለአባገዳዎች ከሰጡት  የሸኔ አባላት መካከል ኤዳኦ ገመዳ በሰጠው አስተያየት፤  ከሽብር ቡድኑ ጋር ተቀላቅሎ በመንቀሳቀሱ እንደተጸጸተ ተናግሯል።

ሸኔ ለኦሮሞ ህዝብ መብትና ጥቅም መከበር ሳይሆን የአሸባሪው ህወሓት ተላላኪ መሆኑን እንደተረዳም ገልጾ፤ በተሳሰተ አመለካከት ቡድኑን ተቀላቅለው ያሉ ወደ ህዝቡ ተመልሰው ሰላማዊ ህይወታቸውን እንዲመሩ ጥሪ አቅርቧል። 

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም