አሸባሪው ህወሃት በንድፈ ሃሳብ ያፈረሳትን አገር በተግባር ለመድገም የሚያደርገው ጥረት አይሳካም

87

ህዳር 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) "አሸባሪው ህወሃት በንድፈ ሃሳብ ያፈረሳትን አገር በተግባር ለመድገም የሚያደርገው ጥረት ፈፅሞ አይሳካም" ሲሉ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን ተናገሩ።

አገር ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ያለው የአሸባሪው ታጣቂ ሃይል በመንዝና ይፋት ተራሮችና ሸለቆዎች እየተቀበረ ይገኛል። 

አሸባሪው ህወሃት በአሁኑ ወቅት ወረራ የፈጸመው አማራና አፋር ክልሎች ቢሆንም የመጨረሻ ግቡ ግን ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው።

በጀግኖች ደምና አጥንት ተገንብታ የቆየችውን ታሪካዊ አገር የማፈራረስ ህልሙን ለማሳካት ከጥፋት አጋሮቹ ጋር ሆኖ እየሞከረ መሆኑንም ተናግረዋል።

"ሆኖም ኢትዮጵያዊያን የሚዝል ክንድ፤ የሚበታተን ህብረት ስለሌለን በጋራ ክንዳችን አሸባሪውን ድል እናደርገዋለን" ብለዋል።

የአሸባሪው ህወሃት የተደበቀ ማንነት ሴራ፣ እርስ በርስ ማጋጨት፣ አሉባልታ እና ክህደት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ንጉሱ በቅርቡ በማይካድራና ጋሊኮማ እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎች በንጹሀን ላይ የፈፀመውን ጭፍጨፋ ለማሳያነት ጠቅሰዋል።

"ጀግናውና ባለታሪኩን የሸዋ ህዝብ በማዋረድ አገር ለማፍረስ በአካባቢው ጦርነት የከፈተው አሸባሪው የህወሃት ወራሪ ሃይል በመንዝና ይፋት ተራሮችና ሸለቆዎች እየተቀበረ ይገኛል" ብለዋል።

በኢኮኖሚና በስነ ልቡና ሊያንኮታኩተው የመጣውን ወራሪ ሃይል በመደምሰስ ህዝቡ የተለመደ የአርበኝነት ታሪኩን እያሳየ መሆኑንም ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሃት ከሰላሳ ዓመት በፊት የተደበቀ አገር የማፍረስ አጀንዳውን ይዞ መምጣቱን ያስታወሱት አቶ ንጉሱ፤ በወቅቱ የሸዋ ህዝብ ያደረገው ተጋድሎ ከፍ ያለ እንደነበር አስታውሰዋል።

በመሆኑም የሽብር ቡድኑ የቆየ ቂሙን ለመበቀልና ህዝቡን ለማዋረድ ዳግም እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ እየተመከተ መሆኑን ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሃት ትልቁ የጦርነት ስልቱ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በመሆኑ ይህንን ስልት በመጠቀም ዛሬም ሽብር እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመው፤ "ህዝቡ አሉባልታና የሽብር ቡድኑ መገለጫ መሆኑን ማጤንና መመርመር አለበት" ሲሉ አስገንዝበዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም