''ቅድሚያ ለዘማች ቤተሰብ!''

67

ባህር ዳር ህዳር 10/2014 (ኢዜአ) በአንዳንዶቹ ቀበሌዎች ''ቅድሚያ ለዘማች ቤተሰብ!'' በሌሎቹ ''ከራሴ በፊት ለዘማች ቤተሰብ!'' የሚሉት መርሐ ግብር ከስያሜዎቹ መካከል ናቸው ።

በክልሉ ከ158 ሺህ በላይ ሕዝብ እየተሳተፈባቸው ያሉት መርሐ ግብሮች እነዚህንና መሰል ስያሜዎች ተሰጥቷቸዋል። በዕለት ወይም በሳምንት በተወሰኑ ቀናት ይተገበራል።

ትግበራው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ነው።

ዓላማው አሸባሪውን ህወሓት የሚፋለሙትን የዘማቾች ቤተሰቦች ሰብል የሚሰበስብበት መርሐ ግብር ነው።

በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ የኩመር አፍጥጥ ቀበሌው አርሶ አደር ግርማው መኳንንት በ''ቅድሚያ ለዘማች ቤተሰብ'' መርሐ ግብር ማክሰኞና ሐሙስ ወደ ግንባር የዘመቱ ሚሊሺያዎች ሰብል እየሰበሰቡ መሆኑን አስታውቀዋል።

እስካሁንም የስምንት ሚሊሺያዎችን ሰብል መሰብሰባቸውንና በቀጣይም የሌሎች ሚሊሺያዎችን ሰብል እንደሚሰብስቡ ተናግረዋል።

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ አዛኑ በላይ ባለቤታቸው ወደ ግዳጅ የሄዱትን ሰብል የአካባቢው ነዋሪዎች ቅድሚያ ሰጥተው እንደሰበሰቡላቸው ተናግረዋል።

የአካባቢው ኅብረተሰብ በሁለት ሄክታር መሬት የለማ የሰሊጥ ሰብል የሰበሰበ ሲሆን፤ በአንድ ሄክታር መሬት የለማ ጤፍ ከራሳቸው አስቀድስመው ሰብስበውልኛል ብለዋል።

በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር የሟቃት ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ጠጂቱ መንግሥቴ''ከራሴ በፊት ለዘማች ቤተሰብ!'' በሚል መርህ የአካባቢው ማህበረሰብ በግማሽ ሄክታር መሬት ያለሙትን የጤፍ ሰብል በወቅቱ አጭደው እንደሰበሰቡላቸው ገልጸዋል።

የአካባቢው ህብረተሰብና አስተዳደር ሰብላቸውን ከመሰብሰብ በተጨማሪ ለቤተሰባቸው እንክብካቤ እያደረገልን ነው ብለዋል።

በአማራ ክልል አሸባሪውን የህወሓት ወራሪ ቡድን የሚፋለሙት የሚሊሺያ አባላት በ2013/14 የምርት ዘመን ያለሙት 13 ሺህ 720 ሄክታር ሰብል ቅድሚያ ተሰጥቶት በመሰብሰብ ላይ መሆኑን የሚናገሩት የቢሮው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ አሻግሬ እንዳየን ናቸው።

ዘማቾቹ የህልውና ዘመቻን ከመቀላቀላቸው በፊት በ20 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ ሰብል አልምተው እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን እየተሰበሰበ ያለው ቀድሞ የደረሰው ሰብል ነው።

ከተሰበሰቡት ሰብሎች መካከልም ጤፍ፣ ገብስ፣ ሰሊጥና በቆሎ ይገኙበታል።

በቀጣይም 6ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚገኘው የዘማቾቹ ሰብል እንደሚሰበሰብ ባለሙያው አስታውቀዋል።

''ለአገርና ወገን ቅድሚያ በመስጠት አሸባሪውን ቡድን ግንባር እየተፋለሙ ለሚገኙ ጀግኖችችን ቤተሰቦች ሰብላቸውን ከመሰብሰብ በተጨማሪ ሌሎች አስፈላጊ ወገናዊ እገዛዎች ተጠናከረው ይቀጥላሉ''ብለዋል።

በአማራ ክልል በ2013/2014 ምርት ዘመን  በ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ  የለማው ሰብል ቅድሚያ ለዘማቾችን በመስጠት ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ጉዳት እንዳይደርስበት እየተሰበሰበ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም