ሙስሊሙ የአረፋ በዓልን ሲያከብር የተቸገሩትን በመርዳት መሆን አለበት

71
አዲስ አበባ  ነሀሴ 15/2010 ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል አደሃ /አረፋ/ በዓልን ሲያከብር የተቸገሩትን በመርዳትና በመደጋገፍ መሆን እንዳለበት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ።  1 ሺህ 439 ኛው የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል ዛሬ ማለዳ በአዲስ አበባ ስታዲዮም ተከብሯል። የምክር ቤቱ ተወካይ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እንድሪስ ባስተላለፉት መልዕክት ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩትን በማገዝ መሆን አለበት። በጋራ ለመኖር ልዩነቶችን ማጥበብ እንደሚያስፈለግ ገልጸው አንድነትን የሚፈታተኑ ተግባራትን ማውገዝ እንደሚገባም አሳስበዋል። አለመግባባትና ቅራኔን በማስወገድ ከመንግሥት ጎን በመቆም ልማቱን ማገዝ ያስፈልጋልም ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ሙስሊም ተቋማዊ ለውጥ አንድነት ኮሚቴ ተወካይ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በበኩላቸው አንድነት ለማምጣት እያንዳንዱ ሙስሊም ኃላፊነት እንዳለበት ተገንዝቦ መስራት አለበት ብለዋል።      በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ የቆየው ልዩነት እንዲያበቃ የሰሩ አካላትን አመስግነዋል።  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአንድነትና በጋራ ብልጽግና ላይ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ኢንጂነር ታከለ አረጋግጠዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም