የተሳሳተ፣ የሐሰትና ሚዛናዊነት የጎደለው ዘገባዎችን ለሰሩ አራት የሚዲያ ተቋማት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ

125

ህዳር 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና የህዝቦችን በጋራ መኖር በሚጎዳ መልኩ የተሳሳተ፣ የሐሰትና ሚዛናዊነት የጎደለው ዘገባዎችን ለሰሩ አራት የሚዲያ ተቋማት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ሚዲያዎቹ የሚሰሩትን የዘገባ ስራ ሲከታተል እንደነበረም ገልጿል።

የጽሁፍ ማስጠንቀቂያው የተሰጣቸው ቢቢሲ፣ አሶሺየትድ ፕሬስ፣ ሲኤንኤን እንዲሁም ሮይተርስ ሲሆኑ ተቋማቱ የሃሰት ዜና በመፈብረክና የተዛባ መረጃ በማሰራጨት ድርጊት ውስጥ እንደተሳተፉ አመልክቷል።

በተለይም የህግ ማስከበር ስራው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሚሰሯቸው ዘገባዎች ችግር እንዳለባቸው በተደረገው ክትትልና ትንተና መረጋገጡን ገልጿል።

ዘገባዎቹ አሸባሪውን ህወሃት የሚደግፉ እንዲሆኑ መደረጉንም አመልክቷል።

በተለይም የህግ ማስከበሩን ተግባር ‘የዘርማጥፋት’ ድርጊት አስመስለው ለማቅረብ መሞከራቸው ተገቢነት እንደሌለው በመግለጽ ድርጊቱን ኮንኗል።

መንግስት የሰብዓዊ ቀውስ ችግርን ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት ዝቅ አድርጎ መመልከት የሚዲያዎቹ ዘገባ ላይ የታየ ችግር እንደነበር የገለጸው ባለስልጣኑ፤ መንግስት ረሃብንና አስገድዶ መድፈርን እንደጦር መሳሪያ ተጠቅሟል የሚል የሀሰት ውንጀላ ድረስ የዘለቀ የተሳሳተ ዘገባ መስራታቸውን አብራርቷል።

በአገሪቱ ዋና ዋና ተቋማት ላይ የስም ማጥፋት ዘገባ መስራታቸውንም አመልክቷል።

በዘገባዎቹ የአገሪቱን መሪ ስም በማጉደፍ አገሪቱ ያልተገባ የዲፕሎማሲያዊ ጫና ላይ እንድትወድቅ መደረጉን ባለስልጣኑ በጻፈው የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ አመልክቷል።

የሚዲያ ተቋማቱ ከዚህ ከጋዜጠኝነት ስነምግባር ካፈነገጠ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ሊታቀቡ እንዳልቻለ ገልጿል።

በመሆኑም ባለስልጣኑ የኢትዮጵያ ህዝብ በሀሰተኛና በተዛባ መረጃ ጉዳት እንዳይደርስበት የመከላከል ሃላፊነቱን ለመወጣት ተቋማቱ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለማሳሰብ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም