በአዮዲን የበለጸገ ጨው አቅርቦት 92 በመቶ ደርሷል

162

ህዳር 10/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ለኅብረተሰቡ የሚቀርበው በአዮዲን የበለጸገ የምግብ ጨው አቅርቦት 92 በመቶ መድረሱን ኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ገለፀ።

 ከአምስት ዓመት በፊት የወጣውን የአስገዳጅ ደረጃ አፈጻጸም ለመገምገም በቅርቡ በተካሄደ ጥናት መሰረት አዮዲን ያለው የበለጸገ የምግብ ጨው አቅርቦት ጨምሯል።

በባለስልጣኑ የምግብ ደህንነትና ኒውትሬሽን አማካሪ አቶ ወንድአፍራሽ አበራ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለኅብረተሰቡ የሚቀርበው ጨው በአዮዲን የበለጸገ መሆን እንዳለበት በሕግ ተደንግጓል።

በአስገዳጅ ደረጃው መሰረት ኅብረተሰቡ በአዮዲን የበለጸገ ጨው እየተመገበ መሆኑን ለማረጋገጥ በዘጠኝ ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ጥናት ተካሂዷል።

በጥናቱ መሰረትም ኅብረተሰቡ ለምግብ ከሚጠቀምበት ጨው 92 በመቶው የሚያስፈለገው የአዮዲን መጠን እንዳለው ማረጋገጥ ተችሏል።

አሃዙ ከሶስት ዓመት በፊት ኅብረተሰቡ ይጠቀም ከነበረው 88 በመቶ አዮዲን ያለው ጨው አሁን የደረሰበት ደረጃ መልካም መሆኑን ያሳያል ብለዋል አማካሪው።

ለጨው አምራቾች ግንዛቤ መፈጠሩ፣ በመውጫና መግቢያ በሮች ቁጥጥር መደረጉና አሰራሮች መጠናከራቸው ለውጤቱ መሻሻል ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

አቶ ወንድአፍራሽ ኅብረተሰቡ በአዮዲን የበለጸገ ጨው በመመገብ ሊከላከላቸው የሚችላቸውን የጤና እክሎችና ጉዳቶችም ጠቁመዋል።

በአዮዲን የበለፀገ ጨው የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት፣ የነፍሰ ጡር እናቶች ያለ ጊዜያቸው መውለድና ሌሎች ጉዳቶችን መከላከል ያስችላል ብለዋል።

አዮዲንን ከተለያዩ ነገሮች ማግኘት ቢቻልም የተጠቀሱትን ችግሮች ለመከላከል በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀው ጨውን በአዮዲን አበልጽጎ መጠቀም በመሆኑ ኅብረተሰቡ ይህንኑ እንዲጠቀም መክረዋል።

አዮዲን ያለበት ጨው ለገበያ መቅረብ ያለበት ከ3 ኪሎ ግራም ባልበለጠ ማሸጊያ መሆኑን ገልጸው በአነስተኛ መጠን የታሸገውን መጠቀም ይበልጥ ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

በአነስተኛ ማሸጊያ የሚቀርብ ጨው በውስጡ ያለው አዮዲን በቅዝቃዜና በሙቀት እንዳይተን በማድረግ ያለውን ጠቀሜታም አስረድተዋል።

አዮዲን በሙቀት ምክንያት እንዳይተን ተመጋቢው ጨውን ራሱ ጨምሮ መጠቀም ወይንም የሚበስለው ምግብ ከእሳት ላይ ከወጣ በኋላ መጨመር ይመከራል።

በአቀማመጥ በኩልም ደረቅ፣ ቀዝቃዛና ንጹህ ቦታ በማስቀመጥ ጨው በውስጡ ያለውን አዮዲን ሳያጣ ለረዥም ጊዜ መጠቀም እንደሚቻል አማካሪው ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በዓመት እስከ 300 ሺህ ሜትሪክ ቶን በአዮዲን የበለጸገ ጨው የሚያስፈልግ ሲሆን ከ10 በላይ ፋብሪካዎች የሚፈለገውን ምርት በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም