ኢትዮጵያውያን ባላቸው የካበተ እሴት የራሳቸውን ችግሮች መፍታት ይችላሉ

90

ህዳር 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ኢትዮጵያውያን ባሏቸው የካበቱና ጠንካራ እሴቶች የራሳቸውን ችግር መፍታት የሚችሉበት ልምድ አላቸው" ሲሉ የካናዳ ዊልፍሪድ ላውሪየር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር አን ፊትዝ-ጌራልድ ገለጹ።

ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ በሚያራምዱት አቋም የኢትዮጵያውያን ቁጣ እየጎላ መምጣቱንም ፕሮፌሰሯ ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር አን ፊትዝ-ጌራልድ ኢትዮጵያ አሸባሪውን ሕወሓት ጨምሮ ሌሎች የውስጥና የውጭ ሃይሎች በከፈቱባት ጦርነት ፈተና ውስጥ መግባቷን ይገልጻሉ።

ምዕራባውያን ለአንድ ወገን ባደላ የፖሊሲ እይታቸው በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና እያደረጉና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት እየሞከሩ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ከምንግዜውም በላይ አንድ ሆነው የገጠማቸውን ፈተና ለመሻገር በጋራ መቆማቸውን በተግባር እያሳዩ እንደሆነ ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያውያን በቆየውና በዳበረው ማህበራዊ እሴቶቻቸው ችግራቸውን በራሳቸው መፍታት ይችላሉ" ብለዋል።

"ጨዋነት፣ ሰብአዊነት፣ መልካምነትና ክብር የኢትዮጵያ መገለጫዋ ነው፤ እነዚህ እሴቶች በሁሉም ማህበረሰብ ውስጥ ሰርጸው መግባትና መጠናከር አለባቸው" ብለዋል ፕሮፌሰር አን።

የዴሞክራሲን መንገድ ይበጀናል በማለት ድምጻቸውን የሰጡ ኢትዮጵያውያን ፍላጎት ሊከበርና ሊጠበቅ እንደሚገባም አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ማህበረሰብ ተኮር የሆነ ብሔራዊ ውይይት መደረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል።

የብሔራዊ ደህንነት እና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይም መንግስት ቀዳሚ ትኩረት አድርጎ መስራት እንዳለበትገልጸዋል።

"ምዕራባውያን አገራት በተለይም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታራምደው አቋም ኢትዮጵያንን አስቆጥቷል" ያሉት ፕሮፌሰር አን፤ "በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በውጪ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ምዕራባውያኑ በአገሪቱ ላይ የሚከተሉትን ፖሊሲ በመቃወም የሚያሰሙት ድምጽ ጨምሯል" ብለዋል።

በተለይም በአሜሪካ የሚኖረው የዳያስፖራ ማህበረሰብ የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ በሚከተለው ፖሊሲ ከፍተኛ ቁጣውን እያሰማ መሆኑንና ይህም በቨርጂኒያ በተካሄደው የግዛት አስተዳደር ምርጫ ላይ በግልጽ መታየቱን ነው የገለጹት።

የአንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በአፍሪካ ላይ ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም የሚጠቀሙት ስትራቴጂ "የአጭር ጊዜ ጥቅምን መሰረት ያደረገ፣ በጣም አደገኛ እና አፍራሽ ነው" ሲሉም ፕሮፌሰር አን አብራርተዋል።

አካሄዳቸውም በአፍሪካ አገራት መካከል የሻከረ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ እንዲሁም የአፍሪካ አገራት የልማት ግቦቻቸውን እንዳያሳኩ እና እንዳያድጉ ማድረግ መሆኑን አመልክተዋል።

በቅርቡ በኢትዮጵያ የምዕራባውያን አገራት ጣልቃ ገብነትን በመቃወም የተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎች ያስተላለፉት መልዕክት ጠንካራ ነው ያሉት ፕሮፌሰር አን፤ ሰልፎቹ ሌሎች ድምጻቸውን እንዲያሰሙ መንገድ በመክፈቱ መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።

"ለውጥ እስኪመጣ ድረስም ኢትዮጵያውያን እና አፍሪካውያን ድምጻቸውን ማሰማት መቀጠል አለባቸው" ብለዋል። 

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም