የደቡብ ክልላዊ መንግስት በደብረ ብርሃን ጊዜያዊ መጠለያዎች ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ አደረገ

55

ደብረ ብርሃን ፤ህዳር 9/2014(ኢዜአ)የደቡብ ክልላዊ መንግስት በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ጊዜያዊ መጠለያዎች ለሚገኙ ወገኖች 10 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉን የክልሉ የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ  ለሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ወልደአማኑኤል አስረክበዋል።

የክልሉ መንግሥት ካደረገው ድጋፍ ውስጥ 900 ኩንታል ስንዴና 200 ኩንታል የጤፍ ዱቄት እንደሚገኝበት ተገልጿል።

እንዲሁም 9 ሺህ 800 ሊትር የምግብ ዘይት ጨምሮ ሌሎች ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶች በድጋፉ እንደተካተቱበትም ተመልክቷል።

ክልሉ ወገኖቻችን ላይ የገጠመው ችግር በዘላቂነት እስኪፈታ ድጋፉን እንደሚቀጥል አቶ ተፈሪ አስታውቀዋል።

ምክትል ዋና አስተዳዳሪው፤ ክልሉ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በፈጸመው ወረራ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር እያደገ በመሆኑ ሌሎች አካላትም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ከሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች በወረራው የተፈናቀሉ ከ218 ሺህ በላይ ወገኖች በደብረ ብርሃንና አካባቢው ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ  ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም