በኢትዮጵያ በቀጣይ አምስት ዓመታት ጥራትን መሰረት ያደረገና ዘመኑን የዋጀ የትምህርት ስርዓት እንዲኖር ትኩረት ተደርጎ ይሰራል

58

ህዳር 9/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በቀጣይ አምስት ዓመታት ጥራትን መሰረት ያደረገና ዘመኑን የዋጀ የትምህርት ስርዓት እንዲኖር በትኩረት እንደሚሰራ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን አስመልክቶ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ማህበረሰብ ጋር ወይይት አካሂዷል።  

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ  በዚህን ወቅት እንዳሉት የመማር ማስተማሩን ስራ ከፖለቲካ አመራሩ ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆኖ መከናወን አለበት።

በዘርፉ  ስር ሰዶ የቆየው የትምህርት ጥራት ችግር ኢትዮጵያ አሁን ለገጠማት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት መሆኑንም ነው ያስረዱት ።

በመሆኑም ጥራትን መሰረት ያደረገ የትምህርት ስርዓት ገቢራዊ በማድረግ ትውልዱን ማዳን ለነገ ይደር የሚባል ስራ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀጣዩ  አምስት ዓመታት ጥራትን መሰረት ያደረገና ዘመኑን የዋጀ የትምህርት ስርዓት እንዲኖር በትኩረት እንደሚሰራ በመጠቆም።

በዚህም ዩኒቨርሲቲዎች በዘርፉ ያለውን ችግር ጥናትን መሰረት በማድረግ እንዲፈታ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባም ነው ሚኒስትሩ ያነሱት፡፡

የትምህርት ጥራት ላይ ያለውን ችግር በመፍታት ትውልድ የማፍራት ስራ ከዛሬ መጀመር እንዳለበትም አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ፕሬዝዳት ፕሮፈሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው ለትምህር ጥራት መውደቅ ስር ሰዶ ከቆየው  ከፖለቲካ አመራሩ ጣልቃ ገብነት ባሻገር አቅምን ያላገናዘበ የትምህር ተቋማት መስፋፋት ዋነኞቹ ምክንያቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ለትምህርት ተቋማት ለማስፋፋት በተሰጠው ትኩረት ልክ  በዘርፉ ያለውን የሰው ሃይል ማብቃት ላይ ሊሰራ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎችም የትምህርት ጥራት ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት በርካታ ዓመታት የፖለቲካ አመራሩ  በዘርፉ ላይ ጣልቃ ሲገባ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህም ለትምህርት ጥራት መጓደል መክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች በተሻለ ነጻነት የሚሰሩበት ስርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡

ውይይቱ በሌሎች ዩንቨርሲቲዎች እንደሚቀጥልም በመድረኩ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም