የኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ ዝም ብለን አናይም

85

ህዳር 9/2014 (ኢዜአ) "የኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ ዝም ብለን አናይም" ሲሉ የመከላከያ ሰራዊቱን የሚቀላቀሉ ወጣቶች ተናገሩ፡፡
”በህይወትና በአካል መስዋትነት የተገነባችው ሀገር እኛ እያለን  አትፈርስም ”በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ የተለያዩ መቋቋሚያ ማዕከላት የሚገኙ ወጣቶች የደም ልገሳ ፕሮግራም  አካሂደዋል፡፡

በደም ልገሳ መርሃ ግብሩ ከተሳተፉ ወጣቶች መካከል የመከላከያ ሰራዊቱን ለመከላከል ዝግጁ የሆኑ ወጣቶች ለኢትዮጵያ ህልውና መጠበቅ ሁለም ዜጋ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

እኛ እያለን አገር አትፈርስም የሚሉት ወጣቶቹ ፤መከላከያ ሰራዊቱን በመቀላቀል የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ወጣት አሰፋ አለማየሁ፤ ኢትዮጵያ ላይ በአሸባሪው ህወሓት ሀይል የተቃጣውን ጥቃት ለመመከት በጦር ሜዳ ከሚደረገው ተጋድሎ ባሻገር ሁሉም ዜጋ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ማድረግ ይገባዋል ብሏል።

ከዚህ በፊት ከቀድሞ ሰራዊቱ በክብር መሰናበቱን አስታውሶ፤ መከላከያ ሰራዊቱን በመቀላቀል ኢትዮጵን ህልውና ለማስጠበቅ መወሰኑን ተናግሯል፡፡

ወጣቶች በተለያዩ ማህበራዊ መዲያዎች በሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች ሳይሸበሩ አካባቢያቸውን ነቅተው እንዲጠብቁም ነው ጥሪ ያቀረበው፡፡

ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ህልውና መጠበቅ በአንድ ዓላማ መሰለፍ እንዳለባቸው የገለጸው ደግሞ ወጣት ካሳሁን በላይ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት መከላከያውን ከመቀላቀል በተጨማሪም ሁሉም ወጣት አካባቢውን በንቃት መጠበቅ ይጠበቅበታል ነው ያለው።

ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት አበበ አለማየሁ በበኩሉ ፤ ለሀገሩ ያለው ፍቅርና ቁጭት ለመዝመት እንዲዘጋጅ ማድረጉን ጠቅሶ፤ ''ሀገር ስትደፈርና ሉአላዊነቷን ስታጣ ዝም ብሎ የሚያይ ወጣት የለም'' ነው ያለው።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ፤ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሀና የሺንጉስ በተለያዩ  ማእከላት ያሉ ወጣቶች የህልውና  ዘመቻውን ለመቀላቀል መወሰናቸውን ገልፀዋል።

በተጨማሪም የአንድ ቀን የምግብ ወጪያቸውን ለመከላከያ ሰራዊቱ በመለገስ እና ደም በመስጠት ለሀገራቸው  የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡

ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላም ነቅተው በመጠበቅ ለህልውና ዘመቻው ስኬት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም