የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላትን መብት የሚጋፋ አይደለም

96

ህዳር 9/2014/ኢዜአ/ ኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገችው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላትን መብት የሚጋፋ አለመሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።
አምባሳደር ዲና በሰጡት ሣምንታዊ መግለጫ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊነት በዋናነት የአገሪቱን ሉዓላዊነትና ነጻነት ለመጠበቅ ነው ብለዋል።

ይሁንና አንዳንድ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት የአዋጁ አተገባበር የዲፕሎማቲክ መብታችንን ይነካብናል በሚል ቅሬታ ማቅረባችውን ገልጸዋል።

በአዋጁ አተገባበር ሂደት አንዳንድ ክፍተቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመው በመሠረታዊነት ግን አዋጁ የዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ መብትን የሚጋፋ አለመሆኑን አረጋገጠዋል።

በሌላ በኩል አንዳንድ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ከአንዳንድ የምዕራባውያን አገራት ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ላይ የሥነ-ልቦና ጦርነት መክፈታቸውን ገልጸዋል።

የመገናኛ ብዙኃኑ በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ወደ ጎን በማለት መሬት ላይ የሌለ የሐሰት መረጃ በተቀነባበረ መልኩ እያሰራጩ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሚዲያዎቹ የሚያደርጉት አንድም የራሳቸውን አገር አልያም ደግሞ የምዕራባውያኑን ድብቅ ፍላጎት ለማስፈጸም መሆኑ በግልጽ እየታየ እንደሆነ ተናግረዋል።

በምዕራባውያኑ የመገነኛ ብዙኃን የሚተላለፉት ዘገባዎች ወደ አንድ ወገን ያደላ በመሆኑ ትክክለኛውን አውነታ የሚያሳይ ዘገባ መሠራት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል መንግሥት ወደ ትግራይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ አስተጓጉሏል እየተባለ የሐሰት መረጃ  እየቀረበ መሆኑን ጠቁመው መንግሥት አሁንም በትግራይ ለሚገኙ ዜጎቹ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በአማራ ከልል በችግር ላይ ለሚገኙ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ እንዲቻል የሰብዓዊ እርዳታ በረራ መፈቀዱንም ተናግረዋል።  

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የአገራቸውን እውነታ ለማስረዳት የሚያደርጉት ጥረት የሚበረታታ መሆኑን አምበሳደር ዲና ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም