በክልሉ ለህልውና ዘመቻው ከ120 ሺህ ኩንታል በላይ ስንቅ ግንባር ቀርቧል - ኮሚቴው

90

ባህር ዳር ህዳር 9/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ለህልውና ዘመቻው 120 ሺህ 400 ኩንታል ስንቅ ግንባር መቅረቡን የክልሉ የማህበረሰብ ሃብት አሰባሰብና የስንቅ ዝግጅት ኮሚቴ አስታወቀ።
የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ አስናቁ ድረስ ለኢዜአ እንዳሉት አሸባሪው ህወሀት አማራን ለማጥፋትና ሀገርን ለማፍረስ አልሞ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ወረራ ፈጽሟል።  

"አሸባሪው በወረራ በያዛቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች በርካታ ሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳቶችን  አድርሷል፤ እያደረሰም ይገኛል" ብለዋል።

ወረራውን በመቀልበስ ዜጎችን ከጥፋት ለመታደግ በክልሉ መጠነ ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ወይዘሮ አስናቁ ተናግረዋል።

የአሸባሪው ወራሪ ሀይል በህዝብና በሀገር ላይ ዘግናኝ ግፎችን እያደረሰ መሆኑን ጠቁመው፤ "አሸባሪውን እንዳመጣጡ ለመመከት አስፈላጊው ሁሉ እየተደረገ መሆኑን  ተናግረዋል።

ሰብሳቢዋ እንዳሉት የህልውና ዘመቻውን ለተቀላቀለው የፀጥታ ሃይል በስንቅ አቅርቦት በመደገፍ ህብረተሰቡ ከፍተኛ እገዛና ትብብር እያደረገ ይገኛል።

ከሐምሌ 1 ቀን 2013 እስከ ህዳር 6 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ለህልውና ዘመቻው 120ሺህ 400 ኩንታል ስንቅ በግንባር ለሚገኘው የፀጥታ ሃይል መቅረቡን ተናግረዋል።

ለስንቅ ዝግጅቱ ከህብረተሰቡ፣ ከባለሃብቱ፣ ከመንግስት ተቋማትና ከንግዱ ማህበረሰብ  ሀብት መሰብሰቡን አመልክተዋል።

የተዘጋጀው ስንቅ በሶ፣ ድርቆሽና ሌሎችምንም ደረቅ ምግቦች ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአማራ ክልል ህዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው የጭካኔ ተግባር እየፈጸመ ያለውን አሸባሪው ህወሀት ለማጥፋት የሚደረጉ ሁለንተናዊ ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሰብሳቢዋ አስታውቀዋል።

"ሴቶች ካላቸው ማህበራዊ ሃላፊነት አኳያ አሸባሪው የፈጸመባቸው ግፍ የከፋ ነው"

ያሉት ደግሞ የኮሚቴው አባል ወይዘሮ ትበልጥ መንገሻ ናቸው።

የክልሉ ሴቶች በአሸባሪው ወራሪ ሀይል እየደረሰባቸው ያለው ግፍ ፈጥኖ እንዲቆም የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ለህልውና ዘመቻው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የህልውና ዘመቻው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ የሚያስፈልገው የስንቅ ዝግጅት ሳይቋረጥ ማቅረብ አንዱና ዋነኛው መሆኑን አመልክተዋል።

በአሸባሪው ህወሓት እየደረሰ ያለውን ግፍ ለመቀልበስ የሚታገሉ ሴቶች በርካቶች መሆናቸውን ጠቁመው ሴቶች ስንቅ ከማዘጋጀት በተጨማሪ በግንባር ስንቅ እያቀበሉና እየተፋለሙ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም