የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የኮቪድ መከላከያ ቁሳቁሶች ወደ አገር ወስጥ እንዳይገቡ ተደረገ

83

አዲስ አበባ፣ ህዳር 9/2014/ ኢዜአ/  ባለፉት ሶስት ወራት ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የኮቪድ 19 መከላከያ ቁሳቁሶች ወደ አገር ወስጥ እንዳይገቡ መደረጉን የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ፕላንና ፕሮጀክት ዳሬክተር ቡድን አስተባባሪ አቶ አብዮት አስጨናቂ ባለፉት ሶሰት ወራት ተቋሙ ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ በተለይም ለኢዜአ ገልጸዋል።

እርሳቸው እንዳሉትም ባለፉት ሶስት ወራት ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የእጅ ጓንት፣ ማስክና ያልተፈቀዱ የሙቀት መለኪያዎች እንዳይገቡ ተደርገዋል።

ቁሳቁሶቹ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ሲመጡ በጉምሩክ ኮሚሽን ቁጥጥር ተደርጎ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ መደረጉን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ባለፉት ሶስት ወራት በመቶ ሺዎች ዋጋ ያላቸው መድሃኒቶችና የመዋቢያ ምርቶች የተቀመጠውን መስፈርት ባለማሟላታቸው ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ መደረጉን ገልጸዋል።

ከ220 ሺህ ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መድሃኒቶች የተቀመጠውን መስፈርት ባለማሟላታቸው ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ መደረጋቸውንም ጠቅሰዋል።

ከ326 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ የመዋቢያ ምርቶች ደግሞ የገላጭ  ጽሁፍ፣ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያልተመዘገቡ የመድኃኒትነት ባህሪ ያላቸው ኮስሞቲክሶች እንዳይገቡ መደረጉን ገልጸዋል።

ፀጉር ለማሳደግ፣ ፂም ለማብቀልዳሌና ለሌሎች ያገለግላሉ በሚል ሲሸጡ የነበሩ የውበት መጠበቂያ ምርቶች ህገ-ወጥ ምርቶች በመሆናቸው ከገበያ እንዲሰበሰቡ ተደርገዋል ብለዋል፡፡

ማህበረሰቡ መሰል የውበት መጠበቂያዎችን ከመጠቀም አስቀድሞ የህክምና ባለሙያዎችን እንዲያማክርም አቶ አብዮት አሳስበዋል።

የህብረተሰቡን ጤና ሊጎዱ የሚችሉ ምግብና መጠጦችም እንዲወገዱ መደረጉን ተናግረዋል።

በግብጽ አገር እንደተመረተ ተደርጎ መለያ የተለጠፈበት የኢትዮጵያዊ አስመጪ አድራሻና ስልክ ቁጥር የተፃፈበት ባለ 200 ሚ.ሊ 85 ሺህ 392 ጠርሙስ ጁስ እንዲወገድ ተደርጓል፡፡

420 ኩንታል ጨው በህገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ከምዕራብ ሐረርጌ ዞን ጤና መምሪያና ፖሊስ ጋር በመተባበር ምርቱ እንዲወረስ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በአንድ ሸቀጣሸቀጥ መደብር ውስጥ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ የት እንደ ተመረተ ፣ ከምን እንደተመረተና መቼ እንደተመረተ የማይታወቅ  በዛገ በርሜል የተከማቸ  9 በርሜል ዘይት መያዙን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም