የኢድ አልአድሃ /አረፋ/ በዓል በሐረር በታላቅ ድምቀት ተከበረ

97
ሐረር ነሃሴ 15/2010 የ1439ኛው የኢድ አልአድሃ /አረፋ/ በዓል ዛሬ በሐረር ኢማም አህመድ ስታዲዮም በሰላምና በታላቅ ድምቀት ተከበረ። ወጣቱም ከጥፋት ተልዕኮ እራሱን በማራቅ ሐይማኖቱ የሚያዘውን መልካም ተግባር ማከናወንና አንድነቱን ማጠናከር እንደሚገባውም ተገልጿል፡፡ በዓሉን የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት፣ ሰላምና መቻቻልን በማጠናከርና አንድነትን በማጎልበት  እንደሚያሳልፉት ምዕመናኑ ገልጸዋል። የእስልምና ሐይማኖት ሥርዓትና አስተምህሮት በሚፈቀደው መሠረት በበዓሉ ላይ የታላቁ የሀረር መስጂድ ጁምኣ ኢማም ሼህ ሙክታር ሐጂ ሙባረክ አማካይነት የሶላት ስግደት ስነ ስርዓት ተከናውኗል። የታላቁ የሀረር መስጂድ ጁምኣ ኢማም ሼህ ሙክታር ሐጂ ሙባረክ ''እስልምና ሰላም፣ ፍቅርና የአንድነት፣ አብሮ የመኖርን ባህል የሚያጠናክር እምነት በመሆኑ በዓሉን ስናከብር ምዕመናኑ የተቸገሩ ወገኖቻችንን በመርዳትና በመንከባከብ ማክበር ይኖርብናል'' ብለዋል። የሀገሪቱን ልማትና ሰላምን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ የጸረ ልማት ሃይሎች ተግባር የእስልምና ሃይማኖት አስተምሮት የማይቀበለው በመሆኑ ወጣቱ ሊከላከለው እንደሚገባ አሳስበዋል። ወጣቱም ከጥፋት ተልዕኮ እራሱን በማራቅ ሐይማኖቱ የሚያዘውን መልካም ተግባር ማከናወንና አንድነቱን ማጠናከር እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡ በስፍራው ከተገኙት ምዕመናን መካከል አቶ መሀመድ አደም በሰጡት አስተያየት የእስልምና እምነት የሰላምና ተቻችሎ የመኖር ተምሳሌት ነው፡፡ በመሆኑም በዓሉን የተቸገሩ ወገኖችንና አሳዳጊ የሌላቸው ህጻናትን በመርዳትና ከሌሎች እምነት ተከታይዎች ጋር ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር ባህልን በማዳበር እንደሚያሳልፉት ተናግረዋል። ''ኃይማኖቱ የሚያዘውን የመረዳዳት የመደጋገፍ ባህልን በሚያሳይ መልኩ ከጎረቤቶቼና ረዳት ከሌላቸው ህጻናትና ወገኖቼ ጋር በዓሉን በድምቀት አከብራለሁ'' ያሉት ደግሞ ከከተማው 7 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው ድሬ ጠያራ ወደራ የመጡት ሼህ አብዱረሃማን ዩስፍ ናቸው።   የአገር ፍቅርና አንድነት እየተጠናከረ በመጣበት በአሁኑ ወቅት የራስን ጥቅም ለማስቀደም የሚሞክሩትን አካላት ወጣቱ ሊጠነቀቀውና ተግባሩን ሊያወግዝ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡   በከተማው ኢማም አህመድ ስታዲዮም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት የተካሄደው ሥነ ሥርዓት ሲጠናቀቅ የሙስሊሙ ኀብረተሰብ ኢስላማዊ ስርዓቱን በጠበቀ ሁኔታ ፈጣሪውን በማመስገን ወደ ቤቱ ተመልሷል። በተመሳሳይ በዓሉ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በ20 ወረዳዎችና 4 የከተማ አስተዳደር በሰላምና በታላቅ ድምቀት መከበሩን የዞኑ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገልጿል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም