የሀሰት መረጃዎች መስፋፋት እና የኢትዮጵያ እውነት

149

ከከሰሞኑ አንዳንድ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን አዲስ አበባ በአሸባሪው ህወሃት እንደተከበበች በመግለጽ የቆየ ምስል በመጠቀም ጭምር የውሸት ዘገባ ሲሰሩ መክረማቸው ይታወሳል።

ሲኤንኤን እና ሌሎችም ሁኔታውን አጋነው ሲዘግቡ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ተጣምረው አብረዋቸው የሚሰሩት ሃይሎች ደግሞ በሌላ አቅጣጫ ‘እጅግ አስፈላጊ ስራ ካላቸው ውጪ ሌሎች ዜጎቻችን’ ኢትዮጵያን ለቃችሁ ውጡ በማለት ውሸቱን እውነት የማስመሰል ሽፋን ሲሰጡ ቆይተዋል።

ይህን ካደረጉት መካከልም በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አንዱ ነው። የሃሰተኛ መረጃዎች ስርጭትና የኢትዮጵያ እውነታ ላይ በኒውስ 24 ላይ የፃፉት ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ “ሁኔታው በአሜሪካ አይን ሲታይ አስገራሚ አይደለም” ብለዋል።

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት መጀመሪያውኑ ለአሸባሪው ህወሃት ድጋፉን ሲያሳይ መቆየቱንና ወደ አዲስ አበባ  የታሰበው ግሰጋሴ ግን እንዳልታየ ነው ያሰፈሩት፡፡

አሸባሪው ቡድን ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በተጨማሪ የክልሎች ልዩ ሃይሎችና ሌሎች የጸጥታ አካላት የአሸባሪውን ህወሃት ወረራ ለመግታት እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የሰሜኑ ጦርነት ከአንድ አመት በፊት ሲጀመር የሃሰት መረጃዎችም መጥለቅለቅ መጀመራቸውን ያወሳሉ ፀሃፊው፡፡

ስለ ጦርነቱ ጅማሬ የምእራባውያን ሚዲያዎች ሆን ብለው እውነታውን እንደሚሸፍኑት በተለይም የሰሜን እዝ ባልተዘጋጀበት መጠቃቱን እና አሉ የሚባሉ መሳሪያዎችን መዘረፉን እንደማያነሱ ገልፀዋል፡፡

የሰሜን እዝ ጥቃት በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የሚመራውን የኢትዮጵያን መንግስት በመጣል የሽግግር መንግስት በመመስረት ግስጋሴውን ወደ አዲስ አበባ ለማድረግ መታሰቡን ሁኔታዎች እንደሚያሳዩና በሃገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያሉ የሽብር ቡድኑ ደጋፊዎች  የሚሳካ ሲመስላቸው በየምክንያቱ ፈንጠዝያቸውን ሲያሳዩ ቆይተዋል፡፡

የአሸባሪው ህወሃት አፈ ቀላጤዎች መካከል አንዱ የሆነው ፃድቃን ገብረተንሳይ የሰሜን እዙን ጥቃትን በተመለከተ ቀድሞ እራስን ለመከላከል የተወሰዳ እርምጃ እንደሆነ በራሱ ላይ መስክሯል፤ ከወር በፊት የወጣ የአሸባሪውም ዶክመንትም  የጥቃቱን አላማ በግልፅ አስቀምጧል፡፡

የሠብአዊ መብት ጥሰት የትም ይፈፀም መወገዝ እንዳለበት ይታመናል  ያሉት ፀሃፊው፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብአዊ ጉዳዮች ኮሚሽነር በጥምረት ባወጡት ሪፖርት በአሸባሪው የተፈፀሙትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አሳውቀዋል። እንዲሁም የሽብር ቡድኑ አላማ አስፈፃሚ ወጣቶች በማይካድራ የፈፀሙት ዘር ተኮር ጭፍጨፋ በቂ ሽፋን ሳይሰጣቸው ቆይቷል፡፡

በአሜሪካን መንግስት መሪነት አብዛኞቹ የምዕራብ ሃገራት መንግስታት ወገንተኝነታቸውን ለአሸባሪው ቡድን ሲያሳዩ በተለይ በአሜሪካ ያሉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎችና ጥቂት የኢትዮጵያ ወዳጆች (ጆንአቢንክ፣ ጄፍ ፒርስ፣ ላውረንስ ፍሪማን) አማካኝነት የኢትዮጵያ ድምፆች በመሆናቸው ይመሰገናሉ፡፡

በቅርቡም ለኢትዮጵያ ድምጻቸውን ከሚያሰሙ ጋዜጠኞች መካከል ሄርሜላ አረጋዊ በውጪ ሚዲያዎች የሚታየውን ወገንተኝነት  በመመከት ስለእውነት በመቆሟ ትመሰገናለች፡፡

የአሸባሪው ቡድን አዲስ አበባ ለመግባት ማለሙ የማይሳካባቸውን ሁኔታዎችን ያስቀመጡት ፀሃፊው 2021 እንደ 1991 አይደለም በማለት ነው፤ አሁን ላይ ከኤርትራ ጋር የከረረ ፀብ ውስጥ የሆነው አሸባሪው ከአማራ ህዝብ ጋርም ቁርሾ ውስጥ ገብቷል፣ እንዲያውም የማያባራ ቀውስ ውስጥ ለመግባት ከአማራ ምሁራን ጋርም ቂም እንዳለው ይናገራል፡፡

የሽብር ቡድኑ ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት 40 የዩኒቨርስቲ ምሁራንን አብዛኞቹ የአማራ ብሄር ተወላጆች በመሆናቸው ምክንያት ከስራ አባሯቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ባለው ፍለጎት ያሳለፈውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ እንደቀልድ የቆጠረው አሸባሪው በጎ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ቅድመ ሁኔታዎችን በመደርደር የሰላም አማራጩን አሰናክሎታል፡፡

አሸባሪው በትግራይ ለሚቀርበው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መሰናክል በመሆን መልሶ የድርድር ጠረጴዛ ላይ የሚቀርብ ጉዳይም ያደርገዋል፡፡ የተኩስ አቁም እድሉን ባለመጠቀምም የአማራና አፋር ክልሎች ላይ ወረራ በመፈጸም መጠነሰፊ ጉዳት አድርሷል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ የመረጠው የጦርነት አቅጣጫ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ ጉዳትን ማስከተል የጀመረው በትግራይ ክልል ነው። ከዛም በወረራቸው የአማራና አፋር ክልሎች አርሶ አደሮችን፣ አርብቶ አደሮችንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ወጣቶችንና ህጻናትን ሳይቀር ገድሏል፡፡

በወረራ በገባበት ኮምቦልቻ ከተማ 100 ወጣቶችን መረሸኑም የጭካኔው ልክ ማሳያ እንደሆነም አመላክተዋል።

በአሸባሪው ቡድን በኩል ጦርነቱ ማለቁን በማወጅ ልክ እንደ 1991 የተለያዩ የመንግስት ተቃዋሚዎችን በማሰባሰብ የሽግግር መንግስት በመቋቋም ላይ ነኝ እያለ ነው፡፡

እውነታው ግን ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች የሽብር ቡድኑ ተቃውሞ ገጥሞታል፤ ለአመታት በዘለቀው ዘመነ አገዛዙ በፈጠረው የአስተዳደር ዝንፈት ኢትዮጵያውያን ዳግም እድል እንደማይሰጡትም አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2005 ተካሄዶ በነበረው ምርጫ ተቃዋሚዎች አሸንፈውት የነበረ ሲሆን አሸባሪው ቡድን ውጤቱን ባለመቀበል አሳሪ ህጎችን፣ ሚዲያ ማፈንና ሲቪል ማህበረሰቡን ማሳደድ መለያ ሆኖ ነበር፡፡ ይህን ተከተሎም ተከታታይ አመታት የነበረው የህዝብ አመፅ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድን ወደ ስልጣን አምጥቷቸዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን ኢህአዴግ ፈርሶ የብልፅግና ፓርቲ ሲመሰረት የሚቀርብለትን የአብረን እንስራ ጥያቄ በተደጋጋሚ ባለመቀበል እንዲሁም የፌዴራል መንግስትና የምርጫ ቦርድን ህግ በመተላለፍ የክልል ምርጫ በማካሄድ አፈንጋጭነቱን ማስመስከሩን በጽሁፋቸው ጠቅሰዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም