እየተወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

71
አዲስ አበባ ነሃሴ15/2010 የኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። ፓርቲው በቀጣይ በሁከቱ እጃቸው ያለበትን አመራሮች ለህግ ማቅረብ አለበት ብለዋል። በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት በሰው ህይወትና በመንግስትና በግለሰብ ንብረቶች ላይ ጉዳት ደርሷል። ሁከቱን ተከትሎ ኢሶዴፓ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ አቶ አህመድ ሽዴን የፓርቲው ሊቀ-መንበር  አድርጎ መሾሙ ይታወቃል። አቶ አህመድ ሽዴ በሰጡት መግለጫ የፓርቲው አመራሮች የእርስ በርስ ግምገማ ካደረጉ በኋላ ሶስት የፓርቲው ማዕከላዊ አባላትንና አምስት ስራ አስፈጻሚዎች እንዲታገዱ ተወስኗል። በቀጣይም ከጎሳ መሪዎች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በመነጋገር አዲስ የአመራር መዋቅር እንደሚፈጠር አቶ አህመድ ተናግረዋል። ውሳኔውን በማስመልከት ኢዜአ በጅግጅጋ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ፓርቲው እየወሰደ ያለውን እርምጃ ደግፈዋል። አቶ መሐመድ አብደላ ፓርቲው የወሰደው እርምጃ ትክክል መሆኑን ገልጸው፤ በህገ-ወጥ ድርጊት የተሳተፉ አካላትን ከማገድ በዘለለ ለህግ ማቅረብ እንደሚገባ ተናግረዋል። በፓርቲው ውሳኔ መደሰታቸውንና በቀጣይ የክልሉን ህዝብ የሚወድ አመራር ወደ ሃላፊነት መምጣት እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ አቶ አሪፍ በዱል ናቸው። የቀድሞው አመራር ሰንሰለትና በጥፋት ድርጊቱ የተሳተፉ አካላት በሙሉ ለፍርድ እንዲቀርቡም ጠይቀዋል። አቶ ፉአድ ሃሰን በበኩላቸው በክልሉ ተከስቶ በነበረው ሁከትና ዝርፊያ ላይ የአመራሩ እጅ እንዳለበት በተደጋጋሚ ይነገር እንደነበር አስታውሰው፤ ፓርቲው በከፍተኛ አመራር ደረጃ እርምጃ መውሰድ መጀመሩ የሚደገፍ ነው ብለዋል። ከጉዳቱ መጠን አንጻር አሁንም መጠየቅ የሚገባቸው አመራሮች መኖር እንዳለባቸው የገለጹት አቶ ፉአድ፤ የፓርቲው አመራር በፍጥነት ከክልሉ ህዝብ ጋር ውይይት ማድረግ አለበት ብለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም