የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ከመደበኛ በተጨማሪ በዘመቻ ሊሰጥ ነው

55

አሶሳ ፤ ህዳር 7 / 2014(ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከመደበኛ በተጨማሪ ከህዳር 13 እስከ 22 / 2014 ዓ.ም. በዘመቻ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
በቫይረሱ መከላከል  ላይ ለከፍተኛ አመራሮች የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ዛሬ በአሶሳ ከተማ  ተካሂዷል፡፡

በክልሉ ከመደበኛ በተጨማሪ ከህዳር 13 እስከ 22 / 2014 ዓ.ም. በዘመቻ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ለመስጠት የባለሙያ ሥልጠና እና ሌሎች ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ጤና ቢሮው አስታውቋል።

የጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ፈቃዱ ረጋሳ እንዳሉት፤ ቢሮው በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለማስቆም መከላከል ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ክትባት ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ በመድሃኒቱ ላይ የሚሰራጩ የተሳሳቱ ወሬዎች ፈተና መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከ98 በመቶ በላይ የክልሉ ህዝብ ስለኮሮና ቫይረስ ግንዛቤ ቢኖረውም ቫይረሱን በመከላከል ረገድ መዘናጋቱ አሁንም መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች አብዛኞቹ ክትባቱን አልወሰዱም ነው ያሉት አቶ ፈቃዱ፡፡

በየደረጃው ያለው አመራር፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ሰዎች እና ሌሎችም ክትባት በመውሰድ ጀምሮ ዋነኛ መከላከያ ዘዴ የሆነውን ጭንብል  አጠቃቀም ህብረተሰቡን በማስተማር አርአያ እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ መንግስታዊ ተቋማት የተጣለባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ የሚወጡት የሰራተኞቻቸው እና የተገልጋዮቻቸው ጤንነት ሲጠበቁ ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የአቅም ግንባታ እና ማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ አቶ ጌታቸው ፊሊጶስ ናቸው።  

ተቋማቱ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎች ሲተገብሩ ቆይተው ማቋረጣቸውን ጠቅሰው የመከላከሉን ስራ እንደገና መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በተለይ የተቋማት አመራሮች ራሳቸው ክትባት ከመውሰድ ጀምሮ በስራ ባህሪያቸው ተጋላጭ የሆኑት በመለየት ሠራተኞቻቸው እንዲከተቡ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በግጭት ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ነዋሪዎች የኮሮና መከላከያ ክትባት እና ሌሎችንም የቅድመ መከላከል አገልግሎቶችን እንዲያገኙ የክልሉ መንግስት ከመተከል ኮማንድ ፖስት ጋር ይሰራል ብለዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤  ህብረተሰቡን ከማስተማር ጀምሮ ጤና ቢሮው በሚያከናውናቸው የኮሮና መከላከል እና ህክምና ስራዎችን በመደፍ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ከተደረገላቸው 48 ሺህ ከሚጠጉ ሰዎች መካከል 3 ሺህ 987 ቫይረሱ እንደተገኘባቸውና የ35 ሰዎች ህይወት ማለፉን በወቅቱ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም