የምክር ቤት አባላት የክተት ጥሪውን ተቀብለው ወደ ግንባር ዘመቱ

60

ጎንደር  ህዳር 7/2014 (ኢዜአ) የጎንደር ከተማ አስተዳደር 46 የምክር ቤት አባላት የክልሉን የክተት ጥሪ ተቀብለው ወደ ግንባር በመዝመት አሸባሪ ቡድኑን እየተፋለሙ መሆኑን የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አስታወቁ፡፡

የምክር ቤቱ አባላት የህወሓት የሽብር ቡድንን በጀግንነት ሲፋለሙ ጉዳት ደርሶባቸው በጠዳ የማገገሚያ ማዕከል ውስጥ በህክምና ላይ ያሉ የጸጥታ አባላትን ዛሬ ጎብኝተዋል።፡  

የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አቶ ፀጋው እዘዘው በጉብኝቱ ላይ እንዳሉት፣ የህዝብ ውክልና ያላቸው የምክር ቤት አባላት የክልሉን የክተት ጥሪ ተቀብለው በመዝመት በአውደ ውጊያ ጠላትን እየተፋለሙ ይገኛሉ።

የሀገር ህልውናና የህዝብ ደህንነት አደጋ ላይ በመውደቁ 46 የምክር ቤት አባላት በሚሊሻ፣ በልዩ ኃይልና በመደበኛ ሠራዊት ጭምር ተቀላቅለው አኩሪ ተጋድሎ በመፈጸም የሕዝብ አለኝታነታቸውን በተግባር እያረጋገጡ ነው።

"ቀሪ የምክር ቤት አባላትም የከተማውን ህዝብ በማስተባባርና በማነቃነቅ በስንቅና ትጥቅ አቅርቦት በመሳተፍ የደጀንነት ሚናቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።"

የምክር ቤት አባል አቶ ዘመነ መወሻ በቀጣይም የምክር ቤት አባላት ህዝብ የሰጣቸውን ውክልና ተጠቅመው ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እያደረጉት ያለውን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡

"የኢትዮጵያን ህልውና ለማስቀጠል ትውልዱ እየከፈለ ያለውን የህይወት መስዋዕትነት መቀላቀል ግድ ይላል" ያሉት አቶ ዘመነ፣ ምክር ቤቱ ትውልዱ እየከፈለ ላለው አኩሪ ጀግንነት ዕውቅና ይሰጣል።

"ጎንደር በወራሪው ኃይል ሳትደፈር የቀረችው በህዝቡና በሠራዊቱ የተቀናጀ ርብርብና የጀግንነት ተጋድሎ ነው" ያሉት ደግሞ ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ መራ አብተው ናቸው።

"እኛ የምክር ቤት አባላት ህዝባችን የሰጠን አደራ በማክበር የህይወት መስዋትነት ጭምር በመክፈል ወራሪውን ኃይል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምስ ከፊት እንሰለፋለን" ብለዋል፡፡

የጠዳ ማገገሚያ ማዕከል አስተባባሪ መቶ አለቃ ውብሸት ዮሐንስ እንዳሉት ማዕከሉ በጉዳት ለመጡ የሠራዊት አባላት የህክምናና የእንክብካቤ አገልግሎት እየሰጠ ነው።

የጎንደር ከተማ ህዝብ በማዕከሉ ለሚገኙ የሠራዊት አባላት እያደረገ ያለው ያልተቋረጠ ድጋፍ ጉዳት የደረሰባቸው የሠራዊት አባላት ፈጥነው እንዲያገገሙ እያገዘ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም