የአዳማ ከተማ ሴቶች ለመከላከያ ሠራዊት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ስንቅ አዘጋጁ

62

ህዳር 6/2014(ኢዜአ ) የአዳማ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት 10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ስንቅ አዘጋጁ።

ከከተማዋ አስተዳደር ስድስት ክፍለ ከተሞችና 18 ቀበሌዎች የተወጣጡ ሴቶች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ዛሬ በአዳማ መክረዋል።

በምክክር መድረኩ የአስተዳደሩ ሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ፎዝያ ኢብራሂም "የከተማዋ ሴቶች በራሳቸው ተነሳሽነት ስንቅ በማዘጋጀት እስከ ግንባር ድረስ ሄደን ወድ ህይወቱን ለኛ ሲል እየገበረ ለሚገኘው የመከላከያ ሠራዊታችን አስረክበናል" ሲሉ አሰታውሰዋል።

በከተማዋ አስተዳደር ከሚገኙ ስድስት ክፍለ ከተሞችና 18 ቀበሌዎች የሚኖሩ ሴቶች በራሳቸው ተነሳሽነት ለአራተኛ ጊዜ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ስንቅ ማዘጋጀታቸውን አሰታውቀዋል።

"ሁሉም በአቅሙ ካለው ላይ በመቀነስ እናቶች ከመቀነታቸው በመፍታት ለሀገር መከላከያ ድጋፍ በማድረግ ሀገር ለማዳን የቀረበውን ጥሪ በተግባር እያረጋገጥን ነው"ብለዋል ወይዘሮ ፎዝያ።

አሁን ደግሞ የስንዴ ዱቄት፣ በሶ፣ ዳቦ ቆሎና የገብስ ቆሎ፣እሽግ ውሃና ሌሎችንም የስንቅ ዓይነቶች አዘጋጅተን ግንባር ድረስ ሄደን ለማስረከብ በዝግጅት ላይ ነን ነው ያሉት።

መከላከያን በሰው ሃይል ለማጠናከር እየተደረገ ባለው ጥረት ብዛት ያላቸው ወጣት ሴቶች እንዲቀላቀሉ መደረጉንም አመልክተዋል።

በተጨማሪም ሴቶች የአካባቢያቸውን ሰላም ከማስጠበቅ አንፃር ከሚሊሺያ፣ ፖሊስና ማህበረሰብ አቀፍ የፀጥታ መዋቅር ውስጥ በመደራጀት ቀንና ሌሊት በፀጥታ ማስከበር ስራ መሰማራታቸውን አስረድተዋል።

"የሀገሪቱ ሰላም እስኪረጋገጥ ድረስ የከተማ ሴቶች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላሉ" ብለዋል ።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው፤ አሸባሪው ህወሓት ሴቶችን ጨምሮ ሁሉም ህብረተሰብ ላይ የፈፀመው ግፍ መቼም ቢሆን መርሳት አይቻልም ብለዋል ።

"ወያኔ አሁንም እየተፍጨረጨረ ያለው ዳግም ስልጣን በመቆናጠጥ የለመደውን ዝሪፊያ ለማስቀጠል ነው" ብለዋል።

አሸባሪው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጠላት ነው፤ ባለፉት 27 ዓመታት ሀገርን ለማፍረስ የህዝቦችን አንድነት፣ አብሮነትና ወንድማማችነት በመሸርሸር አደጋ ላይ የጣለ ቡድን መሆኑንም አውስተዋል።

ሸኔ የኦሮሞን ወጣት ሲጨፈጭ፣ ሲዘርፍና ሲገድል ከነበረው አሸባሪው የህወሃት ቡድን ጋር ጥምረት በመፍጠር ከውስጥና ከውጭ ሃይሎች ጋር በመሆን ሀገራችን ለማፍረስ እየተፍጨረጨሩ መሆኑንም አመልክተዋል።

የአዳማ ከተማ ሴቶች በቆራጥነት ከመከላከያ ጎን ቆመው ስንቅ በማቀበልና ግንባር ድረስ መሄድ ደጀንነታቸውን በተግባር እያረጋገጡ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የከተማዋ ሴቶች ቀደም ሲል ስንቅ በማዘጋጀትና ግንባር ድረስ ሄደው ለመከላከያ ማስረከባቸውን ያስታወሱት ከንቲባው፤አሁንም በራሳቸው ተነሳሽነት ከመከላከያ ጎን ሆነው ሀገራቸውን ለማዳን ርብርብ ማድረጋቸውን አበረታተዋል።

የአስተዳደሩ ሴቶች፣ ወጣቶችና ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል በአንድነት ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን አካባቢያቸውን ከመጠበቅ ባለፈ መከላከያን በገንዘብ፣ በጉልበትና በሞራል ማገዛቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ከንቲባው መልዕክት አስተላልፈዋል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም