የቤተሰብ አባላቱ ለወንድማቸው ተስካር ያዘጋጁትን ድግስ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች ምሳ አበሉ

200

ጎንደር፣ ህዳር 6/2014(ኢዜአ) ---በጎንደር ከተማ ሁለት የቤተሰብ አባላት ለወንድማቸው ተስካር ያዘጋጁትን ድግስ በአሸባሪው ህወሓት ከቄያቸው ተፈናቅለው በከተማው መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ከ500 በላይ ወገኖች የምሳ ግብዣ እንዲውል አደረጉ፡፡

የወንድማቸውን የተዝካር ድግስ ለተፈናቀሉ ወገኖች ምሳ እንዲውል ያደረጉት አቶ ትእዛዙ በጋሻውና ወይዘሮ ፋሲካ በጋሻው የተባሉ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ናቸው፡፡

የሟች ወንድም አቶ ትእዛዙ በጋሻው እንደሚሉት ሀገራችን አሁን ባለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ ሰዎች በጦርነት እየሞቱ፣ እየተፈናቀሉና እየተሰደዱ ድግስ ደግሶ ማብላትን ህሊናቸው አይቀበለውም፡፡

"ከሀገር ሰላምና ከህዝብ ደህንነት በላይ ምንም ነገር ከቶ ሊታሰብ አይገባም" ያሉት አቶ ትእዛዙ፣ ለወንድማቸው አማረ በጋሻው የተዘጋጀውን የተስካር ድግስ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች ማዋላቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የቤተሰቡ አባላት ለተስካር ሊያውሉት የነበረውን አንድ በሬ፣ 300 እንጀራና 5 ጀሪካን ጠላ በጎንደር ከተማ በተለምዶ "ቀበሮ ሜዳ" ተብሎ በሚጠራው መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች ድግስ በማዘጋጀት ዛሬ ምሳ ማብላታቸውን ተናግሯል፡፡

በቅርቡ ጋብቻ የሚፈፅመው የልብ ጓደኛውም የሰርጉን ወጪ በከተማው ለሚገኙ ተፈናቃዮች ለማዋል ቃል መግባቱን ነው አቶ ትእዛዙ የገለጹት።

''በዚህ የችግር ወቅት ዜጎች እርስ በርስ የመረዳዳት ባህላችን በማጠናከር በጦርነቱ የተፈናቀሉ ወገኖች መደገፍ ይገባናል'' ያሉት  ደግሞ የሟች እህት ወይዘሮ ፋሲካ በጋሻው ናቸው፡፡

''ያደረግነው የምሳ ግብዣ ሌሎች የከተማው ነዋሪዎች የእኛን አርአያና ፈለግ ተከትለው ድጋፍ እንዲደርጉ በማሰብ ነው'' ሲሉም ይገልጻሉ።

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ ህብረተሰቡ ካለው በማካፈል ከተፈናቃይ ወገኖች ጎን ሊቆም እንደሚገባም ተናግረዋል።

የተስካር ድግሱን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለችግር የተጋለጡ ወገኖች እንዲውል ማድረጋቸውም ታላቅ ደስታና ኩራት እንደፈጠረባቸው ወይዘሮ ፋሲካ አመልክተዋል።

በምሳ ግብዣው ከታደሙ ተፈናቃይ ወገኖች መካከል ወይዘሮ ውዴ ጫካ በበኩላቸው በአሸባሪው የህወሓት ምክንያት ከትግራይ ክልል ተፈናቅለው ከመጡ አንድ አመት እንደሞላቸው ተናግረዋል።

"የወገን ተቆርቋሪ የሆኑ ግለሰቦቹ የወንድማቸውን የተስካር ድግስ እኛን በማብላትና በማሰብ በማሳላፋቸው ተደስቻለሁ" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

''ወገን ለወገኑ አለሁ ብሎ ሲደርስ መልካም ነገር ነው'' ያሉት ደግሞ በመጠለያው የሚኖሩት አቶ ይግዛው ዓለማየሁ ናቸው፡፡

ሀብትና ያላቸው ወገኖች በችግር ላይ የሚገኙትን ተፈናቃዮች በማሰብ በችግራቸው እንዲደርሱላቸውም ጠይቀዋል፡፡

በጎንደር ከተማ አዘዞ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ቀበሮ ሜዳ እየተባለ በሚጠራው ስፍራ በሚገኘው መጠለያ ውስጥ አሸባሪው ህወሓት በለኮሰው ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ከ2ሺህ በላይ አባወራዎችና ቤተሰቦቻቸው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም