የዲላ፣ ዋቻሞና ወራቤ ዩኒቨርሲቲዎች ለአገር መከላከያ ሰራዊት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ

127

ህዳር 06/2014 (ኢዜአ)  የዲላ፣ ዋቻሞና ወራቤ ዩኒቨርሲቲዎች ለአገር መከላከያ ሰራዊት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።

ዩኒቨርሲቲዎቹ ዛሬ በገንዘብና በአይነት ያደረጉት ድጋፍ ከ63 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ነው።

የወራቤ ዩኒቨርሲቲ 3 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ፣ የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ 30 ሚሊዮን 750 ሺህ ብር እንዲሁም የዲላ ዩኒቨርሲቲ 30 ሚሊዮን ብር ነው የለገሱት።

ዩኒቨርሲቲዎቹ የአገርን ህልውና ለማስጠበቅ የሚደረገው ትግል በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም የምዕራብ አዲስ አበባ ዞን ዲስትሪክት ሰራተኞችም ለአገር መከላከያ ሰራዊት 85 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል።

የዲስትሪክቱ የቁጥጥር ባለሙያ አቶ ብዙነህ ድንበሩ፤ ሰራተኞች ድጋፉን ያደረጉት በራሳቸው ተነሳሽነት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ የሚደረገው ትግል እስከሚጠናቀቅ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።   

የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ፤ በህልውና ዘመቻው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለመከላከያ ሰራዊቱ ያለውን ድጋፍ በተለያየ መንገድ ማሳየቱን ቀጥሏል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ድጋፍ ሁለንተናዊ አጋርነቱን የሚያሳይ በመሆኑ ለሰራዊቱ ትልቅ ትርጉም አንዳለው ጠቅሰው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በተጨማሪም የዲላና ዋቻሞ ዩንቨርሲቲዎች፤ ለመከላከያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ እና የአይነት ድጋፍ አድርገዋል ።

የዩንቨርሲቲዎቹ ፕሬዝዳንቶች ቢሾፍቱ በሚገኘው የመከላከያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመገኘት ድጋፉን አስረክበዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የሆስፒታሉ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ተገኝ ለታ፤ የሰራዊቱ የጀግንነት ምንጭ ህዝባዊነቱ ነው ፤ኢትዮጵያውያን እያደረጉት ያለው ድጋፍ ለቀጣይ ግዳጅ የሚያነሳሳ እንደሆነም ነው የገለጹት።

የዲላ ዩንቨርስቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ችሮታው አየለ፤ በዛሬው እለት 30 ሚሊዮን የገንዘብ እና ለሆስፒታሉ አገልግሎት የሚውል አልጋና ፍራሽ  ለግሰናል ብለዋል።

ዩንቨርሲቲው ከዚህ በፊትም ለሆስፒታሉ ድጋፍ  ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው ይሕም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

የዋቸሞ ዩንሸርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ በበኩላቸው ድጋፉ ለአራተኛ ጊዜ መካሄዱን ጠቅሰው በዛሬው እለት ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ በገንዘብ እና በአይነት ለሆስፒታሉ አበርክተናል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ ላደረጉት ድጋፍ ብርጋዴር ጀነራል ተገኝ፤ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም