በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ከ53 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ ዕድል ተፈጠረላቸው

2669

ባህር ዳር ነሃሴ 14/2010 በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ከ53 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ ዕድል መፈጠሩን የዞኑ ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች መምሪያ ገለጸ።

በመምሪያው የኢንተርፕራይዞች ምስረታና የስራ ዕድል ፈጠራ ቡድን መሪ አቶ ቦጋለ አያሌው ለኢዜአ እንደገለጹት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የስራ ዕድሉ የተፈጠረው በ3 ሺህ 829 ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ ወጣቶች ነው።

ለወጣቶች የስራ ዕድሉ የተፈጠረው በማኒፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በማዕድን፣ በከተማ ግብርና፣ በአገልግሎትና በንግድ የስራ ዘርፎች ነው።

የስራ ዕድሉን ካገኙት መካከል አንድ ሺህ 677 የሚሆኑት ወጣቶች መንግስት ከመደበው የወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር የ142 ሚሊዮን ብር ብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል።

እንዲሁም ከ116 ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚበልጠው ብር ደግሞ በመደበኛው የብድር ስርዓት ከአብቁተ እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከ28 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጭ የተገነቡ 542 የማምረቻ ሸዶችም ለተደራጁ አንቀሳቃሾች መሰጠቱን አስታውቀዋል።

የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል በእንጅባራ ከተማ በእንጨትና ብረታብረት ስራ የተሰማራው ወጣት ንብረት መንግስቴ በሰጠው አስተያየት በተደረገለት የብድርና  የመስሪያ ሸድ ድጋፍ ታግዞ ኑሮውን ለማሻሻል በመትጋት ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡

ቀደም ሲል የስራ ዕድል ተፈጥሮለት በእንጨት ስራ ተሰማርቶ በመስራት በሚያገኘው ገቢ ራሱን በመቻል ላይ መሆኑን የተናገረው ደግሞ ወጣት ሙሉቀን አየለው ነው።

በዞኑ በ2009 በተለያዩ የስራ ዘርፎች ለተደራጁ ከ51 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።