በድሬደዋ የኦህዴድ አባላትና ደጋፊዎች የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተናገሩ

63
ድሬደዋ ነሀሴ 14/2010 የአካባቢያቸውን ሰላም አስተማማኝ በማድረግ  የለውጥ ጉዞውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ በድሬዳዋ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/ አባላትና ደጋፊዎች ተናገሩ፡፡ አባላትና ደጋፊዎቹ በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ከድርጅቱ አመራሮች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት ለውጡን ተከትሎ በሀገሪቱ እየተስተዋለ ያለው የሰላም፣ የልማትና የአንድነት ጉዞ ተስፋ ሰጪና የሚበረታታ ነው፡፡ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መዳበርና ለፖለቲካ ምህዳር መስፋት ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ የሚገኘውን የአንድነትና የለውጥ ጉዞ ወደ ኋላ ለመቀልበስ የሚሯሯጡ አካላትን ለህግ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡ ከአባላቱ መካከል አቶ ሁሴን ከድር "የአካባቢያቸውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግና ልማትን ለማፋጠን ጠንክረን እንሰራለን "ብለዋል፡፡ በገንዘብና በተለያዩ ስልቶች ለውጡን ለማደናቀፍ ለሚሞክሩ አካላት ዕድል መስጠት እንደማይገባ ጠቁሟል፡፡ "በየአካባቢው በቄሮ ስም  ሰላም ለማደፍረስ የሚሯሯጡ አካላትን ለህግ ማቅረብና ተጠያቂ ለማድረግ ተቀናጅተን እንሰራለን "ያሉት ደግሞ አቶ መሐመድ አብደላ ናቸው፡፡ ሐጂ መሐመድ ጅብሪል በበኩላቸው በድሬዳዋም ሆነ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ለውጡን ወደ ኋላ ለመመለስና ለማጥፋት የሚንቀሳቀሱ አካላትን እንደሚቃወሙ ተናግረዋል፡፡ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት ችግሩን ለመፍታትና ለውጡን ለማፋጠን እንደሚሰሩም  ገልጸዋል፡፡ ወጣቶችን በቀበሌና በመንደር ማደራጀትና  አመራሩም በየጊዜው መድረኮች በመፍጠር  የአካባቢውን ሰላምና  የለውጥ ጉዞ ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ ወይዘሮ መይሙና አህመድ ናቸው፡፡ አቶ አህመድ ሰሊህ በበኩላቸው የኦሮሞ ህዝብ ከሶማሌ ወንድሙ ጋር በሃዘን ፣  በጋብቻና በእምነት ጭምር ጥብቅ ትስስር እንዳለው ጠቁመው " ይህን ትስስር በማደፍረስ ድብቅ ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚፈልጉ አካላትን በጋራ መከላከል ይገባል "ብለዋል፡፡ ውይይቱን የመሩት የድሬዳዋ ኦህዴድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አብደላ አህመድ በየደረጃው የሚገኙ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች የተጀመረውን ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ  አጠናክረው ማስቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ይህ ሲሆን  በፖለቲካው መስክ የተገኘው ድል በምጣኔ ሃብትና በማህበራዊ መስኮች በመድገም የዜጎች እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋጋጥ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠር አመልክተዋል፡፡ የድሬዳዋ ኦህዴድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈጅረዲን ሙሳ በበኩላቸው የትኛውም ተግባርና እንቅስቃሴ ተጠያቂነት ያለበት መሆኑን ጠቁመው  ሁሉም በየተሰማሩበት መስክ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ግንባር ቀደም ሆኖ መንቀሳቀስ እንዳላበት አሳስበዋል፡፡ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ለአካባቢያቸው ሰላም መረጋገጥ እያከናወኑ የሚገኙትን አበረታች ሥራ እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም