በኢትዮጵያ ለስኳር ሕመም ምርመራ የማድረግ ልምድ ዝቅተኛ ነው

92

ህዳር 5/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በብዙ ሰዎች ዘንድ ለስኳር ሕመም ምርመራ የማድረግ ልምድ ዝቅተኛ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የስኳር ሕመም በዓለም ብሎም በኢትዮጵያ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ በርካቶችን ለህመም እየዳረገ ይገኛል።

በኢትዮጵያ 3 ነጥብ 2 በመቶ ዜጎች ከተረጋገጠ የስኳር ሕመም ጋር እንደሚኖሩና 9 ነጥብ 1 በመቶዎቹ በቅድመ ስኳር ሕመም ሁኔታ ውስጥ ያሉ መሆናቸውን ጥናቶች እያሳያሉ።

አብዛኛው ሰው በተለያዩ የሕመም ምክንያቶች ወደ ሕክምና ተቋም መጥቶ ምርመራ ካላደረገ በስተቀር የስኳር ህመም እንዳለበት የማያውቅ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የማይቆርጥ የውሃ ጥም፣ የረሃብ ስሜት፣ ቶሎ ቶሎ የውሃ ሽንት ማስቸገር የቆዳ መድረቅ፣ ድካም፣ ቁስል ለመዳን ረጅም ግዜ መፍጀት፣ እና አይን ብዥታ ሌሎች የስኳር በሽታ ምልክቶች ናቸው።

የስኳር ህመም አይነት (ታይፕ)  አንድ እና ሁለት እንዲሁም በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት በማለት የህክምና ባለሙያዎች በሶስት ይከፍሉታል።

አይነት አንድ የሚባለው የስኳር ህመም ብዙ ጊዜ በልጅነት የሚከሰት ሲሆን ልጆች በሰውነታቸው ውስጥ ኢንሱሊን ሳይመረት በመቅረቱ የሚመጣ በሽታ በመሆኑ ኢንሱሊን በመስጠት ህክምናውን እንዲያገኙ ይደረጋል።

ለዚህም ነው ኢዜአ ያነጋገራት ወጣት ማራኪ ጌታቸው ከዛሬ 8 ዓመት በፊት  ማራኪ ለህክምና ወደ ሆስፒታል በሄደችበት ወቅት የስኳር ሕመምተኛ ሆና የተገኘችው።

በወቅቱ ስለ ህመምሙ እርሷም ሆነ ቤተሰቧ ብዙም ግንዛቤ  እንዳልነበራቸው ትናገራለች።

የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በሚፈለገው ደረጃ ባለመሆኑ ጉዳቱ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መሆኑን ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ ወይዘሮ ማርታ ስለሺ ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ የስኳር ህመምተኞች ማህበር መሥራች አቶ ባዩ ወሰን በበኩላቸው በማህበረሰቡ ዘንድ ስለ ስኳር ህመም ያለው ግንዛቤ እንዲያድግ መስራት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ የስኳር ሕመም ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ጌታሁን ታረቀኝ፤ በሽታውን ለመከላከል ማህበሩ ላለፋት 37 ዓመታት በርካታ ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።

ለሕሙማኑ ኢንሱሊን በስፋት ለማዳረስና የግንዛቤ ማስጨበጫዎች በመስጠት  እየሰሩ ቢሆንም፤  በቂ ባለመሆኑ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን  እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ563 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የስኳር ሕመም እንደለባቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።

የስኳር ሕመም ቀን በዓለምና በአገር አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ ጊዜ "የስኳር ሕመም ሕክምና እና እንክብካቤ ተደራሽነት አሁን ካልተተገበረ መቼ?" በሚል መሪ ሐሳብ  በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም