ኢትዮጵያን በማፍረስ የሽብር ቡድኑን ለማንገስ በግልጽና በስውር የሚደረገው እኩይ ተግባር በፍፁም አይሳካም

79

ህዳር 5/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን በማፍረስ የህውሓትን የሽብር ቡድን ለማንገስ በግልጽና በስውር የሚደረገው እኩይ ተግባር በፍፁም ተቀባይነት የሌለውና የማይሳካ ሙከራ መሆኑን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተደድር ርስቱ ይርዳው ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በቡታጅራ ከተማ መከላከያ ሰራዊትን የሚደግፍ እና የውጭ ጣልቃ ገብነትን በሚያወግዘው ህዝባዊ ሰልፍ ላይ በመገኘት ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም በኢትዮጵያ ተላላኪ መንግስት እንዲኖር ለማድረግ እየሰሩ ያሉ የተለያዩ የውጭ ሃይሎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ሆኖም ኢትዮጵያን በማፍረስ የህውሓትን የሽብር ቡድን ለማንገስ የሚደረገው ሴራና እኩይ ተግባር በፍፁም ተቀባይነት የሌለውና የማይሳካ ሙከራ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ህዝብ አሸባሪ ቡድኑን ለማጥፋት በሚደረግ ሁለንተናዊ ጥረት የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ ስልጣንን በበላይነት ተቆጣጥሮ በቆየባቸው ዓመታት በሀብት ዘረፋ፣ ስርቆትና አሻጥር በርካታ ወንጀሎችን ሲፈፅም መቆየቱን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያውያን በምርጫ ካርዳቸው መሪያቸውን ወደ ስልጣን አምጥተው ልማታቸውን ለማፋጠን መስራታቸው ያላስደሰተው አሸባሪ ሃይል ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰሩ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ''በተባበረ ክንድ እና በአንድነት መንፈስ ተነሳስተን አሸባሪን ቡድኑን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ቆርጠን ተነስተናል'' ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

የኢትዮጵያውያንን አብሮ የመኖር እሴት ለመሸርሸር አሸባሪው ብዙ ቢሰራም የሕዝቦች አንድነትና መተሳሰብ ላይበጠስ የተጋመደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም