የሽብርተኞችን ጥቃት ለመከላከል በምንችለው ሁሉ ከመንግስት ጎን ነን

113

ነገሌ ህዳር 4/2014 (ኢዜአ) የሽብርተኞችን ጥቃት ለመከላከል በሚችሉት ሁሉ ከመንግስት ጎን በመሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ የጉጂ ዞን የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ፡፡

ከዞኑ ወረዳዎች የተውጣጡ 200 የሀገር ሽማግሌዎች ትናንት በነገሌ ከተማ የሰላምና የልማትን ኮንፈረንስ ተካሂደዋል፡፡.

የአገር ሽማግሌዎቹ  "አገራችንን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እየተጋፈጠች በምትገኝበት በዚህ ጊዜ እኛም ከመንግስት ጎን ሆነን የድርሻችንን ማበርከት ግዴታችን ነው" ብለዋል ።

ከአገር ሽማግሌዎቹ መካከል የነገሌ ከተማ ነዋሪ አቶ ኢያ ዋሪዎ "ሀገር ለማፍረው የተነሱ ጠላቶችን ለመፋለም እየተካሄደ ካለው የህልውና ዘመቻ  በተጓዳኝ የሽብር ቡድኑ ህዝብን እንዲዘርፍ ሀገር እንዲያፈርስና በንጹሃን ላይ ጥቃት እንዲያደርስ የሚተባበሩ የውስጥ ባንዳዎችን ማጥራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

ሌላው  የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ፋጤ ዱባ "ሽብርተኛው ሸኔ ከዞኑ ጉሚ ኤልደሎ፣ ሊበን፣ ጎሮዶላና ሰባቦሩ ወረዳዎች የመንግስት ደጋፊ ናችሁ በሚል ንጹሃንን ማፈናቀሉን ቀጥሎበታል" ብለዋል፡፡

መንግስት የሽብርተኛውን ጥቃት ለማስቆምና የህግ የበላይነትን ለማስከበር በሚያደርገው ጥረት ጥቆማ በመስጠት ጭምር ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል ።

"ሽብርተኞቹ ዜጎችን እያፈናቀሉ ያሉት "ይሄን ከተማ ይዘናል ያንንም ልንይዝ ነው" በሚል በሀሰት መረጃ ስለሆነ ልንሸበር አይገባም" ብለዋል፡፡

 "በውስጥ አሸባሪዎችና በውጭ ጫናና ተጽእኖ ሳንረበሽ ሀገራችንንና አካባቢያችንን ነቅተን የመጠበቅ  አቅምም ብቃቱም አለን" ያሉት ደግሞ  አቶ መሀመድ በቸሎ ናቸው።

የኦሮሞ ህዝብ ያሳለፈውን ግፍና መከራ ረስቶ ዳግም በባርነት ለመኖር በሽብርተኛች ህወሀትና ሸኔ  እንደማይመራ አክለዋል።

በመንግስት መወቅር ውስጥ ሆነው መጣብህ ሽሽ የሚሉና የሽብር ቡድኖችን የሚደግፉና ሀገር ለማፍረስ የሚሰሩ እንዳሉ ጠቁመው፤ የፌደራልም ሆነ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የህዝብ ድምጽ ሰምተው ውስጣቸውን እንዲፈትሹና ጠበቅ ያለ እርምጃ እንዲወስዱ አመልክተዋል፡፡

ኮንፈረንሱን የመሩት የኦሮሚያ ክልል ከተማ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጉዮ ገልገሎ "መንግስት ሀገር ለማፍረስ በሚሰሩ የውስጥና የውጭም የጥፋት ሃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል" ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ ከሌላው ወንድም የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን በህይወት መስዋእትነት ያገኘውን መልካም አጋጣሚ በሽብርተኞች ፕሮፓጋንዳ ተታሎ ነጻነቱን አሳልፎ እንደማይሰጥ አረጋግጠዋል።

 ህዝቡ ሀገር ላማዳን እየተካሄደ ላለው የህልውና ዘመቻ የጀመረውን ድጋፍና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

ከመድረኩ ተሳታፊ ሀገር ሽማግሌዎች ለተነሱት ጥያቄዎች በሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም