ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት የአሜሪካ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር በመከባበርና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ሊሰራ ይገባል

57

ህዳር 5 /2014 (ኢዜአ)በቀጠናው የኢትዮጵያን መሪነት ለማረጋገጥ፤ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን የአሜሪካ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር በመከባበርና በጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ ሊሰራ እንደሚገባ የኢትዮጵያ አሜሪካውያን ሲቪክ ካውንስል አመለከተ።

የኢትዮጵያ አሜሪካውያን ሲቪክ ካውንስል የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ እየተከተለ ያለውን የተሳሳተ አካሄድ በማውገዝ ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎች መግለጫ ልኳል።

በመግለጫውም በቅርቡ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይና የመከላከያ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች የተሰጠውን የጣልቃ ገብነት ሃሳብ ተቃውሟል።

አሜሪካ የጦር ሃይሏን በኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ ለማሳተፍ የተነሳውን ሃሳብ ስህተትነት ያስገነዘበ ሲሆን “መላው የአሜሪካ ህዝብም ከአፍጋኒስታን የጆ ባይደን ፖሊሲ ውድቀት በኋላ ይህ በአፍሪካ እንዲደገም አይፈቅድም”ብሏል።

መግለጫው አክሎም በኢትዮጵያ የተከሰተው ግጭት የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ አስተዳደሩ ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን በራሷ እንድትፈታ ሊተዋትና የኢትዮጵያን የውስጥ ችግር የሚያባብሱ ተግባራትን ከማከናወን ሊታቀብ እንደሚገባው አሳስቧል፡፡

የአስተዳደሩ የተሳሳተ ፖሊሲና ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን የማራመድ ሃሳብም በአሜሪካውያን ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጿል።

አሜሪካ ኢትዮጵያን በተመለከተ በመከተል ላይ ያለችውን የተሳሳተ ፖሊሲ ዳግም ማጤን እንዳለባት አሳስቦ፣ ለ118 ዓመታት የቆየውን የኢትዮ-አሜሪካ ወዳጅነት ለማጠናከርና ኢትዮጵያ የቀጠናው ሰላምና መረጋጋት መሪ እንድትሆን ለማስቻል አስተዳደሩ ከኢትዮጵያ ጋር በመከባበርና በጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ ሊሰራ እንደሚገባው አስገንዝቧል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም