"ካናዳ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ግጭት እንዲፈታ ገንቢ ሚና መጫወት ትፈልጋለች"

148

ህዳር 5/2014 (ኢዜአ) ካናዳ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ግጭት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ በፍጥነት እንዲፈታ ገንቢ ሚና መጫወት አንደምትፈልግ የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜላኒ ጆሊ ገለጹ።

በካናዳ የኢትዮጵያ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ትናንት ማምሻውን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜላኒ ጆሊ እና ከካናዳ የቤቶች የብዝሃነትና አካታችነት ሚኒስትር አህመድ ሁሴን ጋር በበይነ መረብ ውይይት አድርገዋል።

ከሚኒስትሮቹ በተጨማሪ በውይይቱ ላይ የካናዳ ፓርላማ አባላት ተሳትፈዋል።

ዳያስፖራዎቹ በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ግጭትና በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉደዮች ጥያቄዎች ተነስተዋል።

የካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜላኒ ጆሊ፤ አገራቸው በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት በቅርበት እየተከታተለች እና ሁኔታዎችን ለመረዳት እየሞከረች መሆኑን ገልጸዋል።

በግጭቱ ምክንያት በንጹሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት እንደሚያሳስባት እና የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።

ካናዳ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ፍላጎት አላት፤ አገራቸውም ገንቢና በጎ ሚና መጫወት ትፈልጋለች ብለዋል።

በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሙሳ ፋቂ ማህማት የሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ሆነው የተሰየሙት የቀድሞው የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚደግፍም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ የገለጹት።

ካናዳ የምትፈልገው የኢትዮጵያ ሰላም መሆን ነው ያሉት ሜላኒ በኢትዮጵያ ሰላም ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶችን በሙሉ ትደግፋለች ብለዋል።

ይህንን ከግምት ውስጥ ያስገባ ውይይትም የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ትናንት በስልክ ውይይት ማድረጋቸውን አንስተዋል።

በግጭቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖችም አስፈላጊውን ሰብአዊ ድጋፍ እንደምታደርግ አመልክተዋል።

ካናዳ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለመረዳት እየሞከረች ነው ያሉት ሚኒስትሯ ችግሩ በፍጥት እንዲቋጭ ትሻለች ብለዋል።

በቅርቡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ ያወጡትን ሪፖርት ካናዳ እንደምተቀበለው እና ሪፖርቱ አድሎ የሌለበት እንደሆነም አመልክተዋል።

በሪፖርቱ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላት በሕግ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ካናዳ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር ትፈልጋለች ያሉት ሚኒስትሩ የሁለቱ አገራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች የትናንት የስልክ ውይይትም ትብብሩን ማሳደግ በሚቻልበት ጉዳይ ምክክር መደረጉን አመልልክተዋል።

የካናዳ የቤቶች የብዝሃነትና አካታችነት ሚኒስትር አህመድ ሁሴን በበኩላቸው አገራቸው የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ለቀጠናው ወሳኝ መሆኑን እንደምትረዳ ገልጸዋል።

በዚህ ረገድም "ካናዳ በቀጠናው አገራት ያላትን እምነት ተጠቅማ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲያገኝ ድጋፍ ታደርጋለች" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ራሷን የምትለውጥበት ምርታማ የወጣት ሃይል እንዳላት እና ባለፉት ዓመታትም "አስገራሚ" የሚባል የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገቧን አውስተዋል።

"የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያን የማሳደግ አቅም አለው፤ የኢትዮጵያ ቀጣይ ጊዜ ብሩህ ይሆናል ብዬ አምናለሁ" ብለዋል ሚኒስትሩ።

ካናዳ ከኢትዮጵያ ጋር በግብርና፣ በአገልግሎት እና በሌሎች ዘርፎች ያላትን ግንኙነት ማጠናከር እንደምትፈልግ እና የትብብሩ መጎልበት የሁለቱን አገራት ዜጎች ተጠቃሚ እንዲያደርግ ትሻለች ብለዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ግጭት በፍጥነት መቋጨት እንዳለበት እና ኢትዮጵያ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ መመለስ እንደሚገባትም አመልክተዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የኢትዮ ካናዳ ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ የኦቶዋ ቻፕተር ምክትል ሊቀ-መንበር አቶ ሰማነህ ታምራት በሰሜን ኢትዮጵያ ለደረሰው ግጭት ዋና መንስኤ ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

የሕወሓት አሸባሪ ቡድን ለ21 ዓመታት በትግራይ ክልል ሲያገለግል በነበረው የአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ  በተኛበት ጥቃት በመፈጸም መኪና ላያቸው ላይ በመንዳት ጭምር በአሰቀቂ ሁኔታ መግደላቸው መንግስት ወደ እርምጃ እንዲገባ እንዳስገደደው አመልክተዋል።

የግጭቱ መነሻ ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ ወንጀል መሆኑን ካናዳን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በውል ሊገነዘበው እንደሚገባም ተናግረዋል።

ካናዳን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሕወሓት አሸባሪ ቡድን በማይካድራ የፈጸመውን አሰቀቃቂ ጭፍጨፋ፤ በአማራ እና በአፋር ክልሎች የፈጸመውን ግፍና በደል ዝም ማለት የለባቸውም ድርጊቱን ማውገዝም አለባቸው ነው ያሉት አቶ ሰማነህ።

ሁለቱም ሚኒስትሮች ይህ የመጀመሪያው ስብሰባ በመሆኑ ውይይቱ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ለመረዳት የሚያስችል እድል የሚፈጥር መሆኑን መረዳታቸውን ገልጸው፤ ለወደፊቱ ሰፋ ባለ ሁኔታ እና ቀጣይነት ባለው መልኩ የጋራ ውይይቶች እንዲሚቀጥሉ በስብስባው ማጠቃላይ ላይ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናንት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ከካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

"ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ለኢትዮጵያ ስላሳዩት ልባዊ ወዳጅነት እና ድጋፍ ጥልቅ ምሥጋና አቀርባለሁ" ብለዋል በመልዕክታቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም