በሶማሌ ክልል ህዝበ ሙስሊሙ የአረፋ በዓልን ሲያከብር የተጎዱና የተፈናቀሉ ወገኖቹን በመርዳት እንዲሆን ጥሪ ቀረበ

65
ጂግጂጋ ነሀሴ 14/2010 ህዝበ ሙስሊሙ የኢደ አል አደሃ (አረፋ) በዓልን ሲያከብር የተጎዱና የተፈናቀሉ ወገኖቹን በመርዳት መሆን እንዳለበት የሶማሌ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሊቀመንበር ሼክ አብዱረህማን ሃሰን ጥሪ አቀረቡ፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙ ለፍቅር አብሮነት እና ሰላም ተግቶ እንዲሰራም ጠይቀዋል። ሼህ አብዱረህማን ሃሰን በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በክልሉ ተከስቶ የነበረው ሁከትና ዝርፊያ በእስልምና አስተምሮ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም፡፡ 'ኢስላም ሰላም ነው' ያሉት ሼህ አብድረህማን፤ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ይህን አስተምሮ ዘወትር ሊጠብቅ እንደሚገባ መክረዋል፡፡ የአረፋ በዓልን ምክንያት በማድረግ ህዝበ ሙስሊሙ በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖቹን መጠየቅ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ በሁከቱ ምክንያት የተዘረፉ ንብረቶች እንዲመለሱ የሃይማኖት አባቶች ተግተው መስራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል። ከጥቂት ቀናቶች በፊት ሁከት ተከስቶባቸው የነበሩ ጅግጅጋን ጨምሮ የሶማሌ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ወደ ቀደመ ሰላማቸው በመመለሳቸው ሕዝበ ሙስሊም ነገ በጋራ በመገናኘት በዓሉን በደማቅ ሁኔታ ያከብራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም