ነፃነትና ክብር ያለመስዋትነት አይገኝም

54

መተማ ፤ ህዳር 4/2014 (ኢዜአ) ነፃነትና ክብር ያለመስዋትነት ስለማይገኝ ተመራቂዎች በምትችሉት ሁሉ እንደ ጀግኖች አባቶቻችን ሃገራችንና ህዝባችን ከተጋረጠበት የህልውና አደጋ መታደግ ይጠበቅባችኋል ሲሉ የአማራ ክልላዊ መንግስት ርዕስ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፍአለ ተናገሩ።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሌጅ ለዘጠነኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን ልዩ ሃይል ፖሊሶች ዛሬ አስመርቋል።

ርዕስ መስተዳደሩ  በምረቃ ሥነ -ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውጭ ሃይሎች ጋር አብሮ  እየሰራ ነው።

ቡድኑ በክልሉ በወረራቸው አካባቢዎች ንፁሃንን ከመግደል ባለፈ የመንግስትና የግል ንብረቶችን ዘርፏል፤ ያልቻለውን እያወደመ ጠላትነቱን በግልፅ ያሳየ የከሃዲ ስብስብ ነው ብለዋል።

የዛሬው ተመራቂዎች ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የወራሪውን እኩይ ተግባር የማስቆምና የመደምሰሱን ተግባር በታላቅ ጀብዱ እንደምትፈፅሙት ክልሉ ሙሉ እምነት አለው ነው ያሉት ዶክተር ይልቃል።

ነፃነትና ክብር ያለ መስዋትነት እንደማይገኝ የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ ተመራቂዎቹም እንደ ቀደሙ ጀግኖች አባቶች ገድል በመፈፀም የክልሉን ብሎም የሃገሪቱን  ነፃነት ማስከበር እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

 ሃገራችንና ህዝባችን የተጋረጠበትን አደጋ መክታችሁ ትታደጉታላችሁ ብለዋል።

''ተመራቂዎች የፖሊሳዊ ስነ ምግባርን በመላበስ በተሰጣቸው ግዳጅ ሁሉ እንደ አርበኛ አባቶች ገድል በመፈፀም የክልሉን ብሎም የሃገሪቱን ህልውና ማስጠበቅ ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው'' ያሉት ደግሞ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ ናቸው።

አሸባሪው የህወሃት  ቡድን ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች ሰዎችን እየገደለ፣ እያፈናቀለና እያጎሳቆለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ድርጊት በአጠረ ጊዜ በማስቆም  ቡድኑ  ባለበት ይደመሰሳል ብለዋል።

የገቢዎች ሚኒስትርና በህልውና ዘመቻው የስልጠና ማዕከላት አስተባባሪ አቶ ላቀ አያሌው በበኩላቸው፤ የአሸባሪው የህውሃት ቡድን ከውጭ ጠላት ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ሃገር የማፍረስ ተግባር እየፈፀመ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ቡድኑ ታሪክ ይቅር የማይለውን በደል በህዝብ ላይ እየፈፀመ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተመራቂዎች ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የአሸባሪውን  እኩይ ተግባር በማክሸፍ  የህዝቡን  ክብር ማስጠበቅ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

አሜሪካን ጨምሮ በአንዳንድ የምዕራባውያን  ሀገራት ሚዛናዊ ባልሆነ ፍርድ ሳንበገር በራሳችን መስዋትነት ነፃነታችንን እንጎናፀፋለን ብለዋል ሚኒስትሩ።

በምረቃው ሥነ ሥርዓት፤ የክልሉ፣ የፌደራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት መገኘታቸው ተዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም