ሽብርተኛው የህወሓት ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያን አያፈርሳትም

67

ህዳር 3 /2014 (ኢዜአ) ለአገራችን ደጀን ነን ያሉ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ሴቶቸ "እኛ እያለን አገራችን አትደፈርም፤ ሽብርተኛው የህወሓት ወራሪ ኃይልም አያፈርሳትም" በማለት ለመከላከያ ሠራዊት ስንቅ አዘጋጅተዋል።

የክፍለ ከተማው ሴት አደረጃጀቶች "እኔም የአገር መከላከያ ሠራዊት ነኝ፤ ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን እቆማለሁ" በማለት ለመከላከያ ሠራዊት ስንቅ በማዘጋጀት ደጀንነታቸው አሳይተዋል።

በስንቅ ዝግጅቱ በሶ፣ ዳቦ ቆሎ፣ የእንጀራ ድርቆሽ እንዲሁም አልባሳት፣ የንጽህና መጠበቂያና ሌሎች ድጋፎችም ተደርገዋል።

ከየወረዳዎቹ ለስንቅ ዝግጅቱ እንዲውል በሳምንት ጊዜ ውስጥ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት ማሰባሰብ እንደተቻለም ተገልጿል።

የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሃቢባ ሲራጅ፤ የሽብር ቡድኑን ህወሓት ተላላኪና ጉዳይ አስፈፃሚዎች ለመቆጣጠርና የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ማህበረሰቡ ሌት ተቀን እያደረገ ያለው ተግባር የሚያስመሰግን መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን ተግባር አጠናክሮ በማስቀጠል የአሸባሪውን ህወሓት ወራሪ እና ተላላኪ ኃይል መንጥሮ በማውጣት ተጠያቂ ማድረግ እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል።

በክፍለ ከተማው የወረዳ 02 ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ አይናለም ግርማ፤ የወረዳው ሴት አደረጃጀቶች ያለማንም ወትዋች በራሳቸው ወጪና ተነሳሽነት ለሠራዊቱ የስንቅ ዝግጅት ማደርጋቸውን ገልጸዋል።

በስንቅ ዝግጅቱ የተሳተፉት ወይዘሮ ሐበሻ ተፈራ፤ "እኛ እያለን አገራችን አትደፈርም" በማለት አኩሪ ጀብዱ እየፈጸመ ለሚገኘው ሠራዊት የስንቅ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ወጣት መስታወት ደጀኔም ደግሞ ሴቶች የአገር ደጀን እንደመሆናችን በአገር ሉዓላዊነት ላይ አደጋ የደቀነውን ሽብርተኛ ኃይል ለማጥፋት መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው ሠራዊት ድጋፍ እያደረግን ነው ብላለች።

"ከሕዝባችን፣ ከመንደራችንና ከራሳችን በምናገኘው ገንዘብ ለሠራዊቱ የምናደረገውን ድጋፍ እናስቀጥላለን" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ቃኒታ ሽፋ ናቸው።

ወይዘሮ በለጡ ሶሬሳም ልጆቻቸው ሠራዊቱን ተቀላቅለው የአገር ሉዓላዊነት እንዲያስጠብቁ ከመላክ ጀምሮ ስንቅና ትጥቅ በማቅረብ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የስንቅ ዝግጅቱ ተሳታፊ እናቶች ለሠራዊቱ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የአገር ሉዓላዊነት በማስጠበቅ አሸባሪውን የህወሓት ወራሪ እና ተላላኪ ኃይል ለመቅበር በየአውደ ግንባሩ ድል እየተቀዳጀ ለሚገኘው ጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልል ልዩ ኃይሎች፣ ፋኖ እና ሚኒሻ ደጀንነቱን ለማረጋገጥ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የስንቅና ትጥቅ ድጋፋቸውን ቀጥለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም