በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ሐሰተኛ መረጃዎች እንዲሰራጩ የሚደረገው ህዝብን ከመንግስት ለመነጠል ነው

124

ህዳር 3/2014 (ኢዜአ) አሜሪካ መገናኛ ብዙሃኖቿን ተጠቅማ በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ሐሰተኛ መረጃዎች እንዲሰራጩ የምታደርገው ሕዝብን ከመንግስት ለመነጠል መሆኑን በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ገለጹ።

ሕወሓት ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ሲጠቀምበት የነበረውን የሀሰት ፕሮፓጋንዳና የመከፋፋል ሴራ አሁንም እየተጠቀመበት መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮ- አሜሪካ የዜጎች ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ ወይዘሮ አስኳል ተፈሪ ከኦ ቢ ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ አሜሪካ በኢራቅና ሊቢያ አገር ለማፍረስ ስትጠቀምባቸው የነበሩ  የሐሰት ትርክቶችን በኢትዮጵያ ላይም ተግባራዊ ለማድረግ እየሞከረች ነው ብለዋል።

ኢራቅ የጅምላ ጨራሽ መሳሪያ አላት ይህ ለኛ ስጋታቸን ነው በማለት ያሰራጩትን የሐሰት መረጃ  ተጠቅመው አሜሪካና አጋሮቿ በኢራቅ ላይ ወረራ ፈጽመው  አገሪቷ አሁን ያለችበት ደረጃ ላይ እንድትገኝ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

አመየሪካ በሊቢያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሞአመር አል ጋዳፊ ላይ ሕዝቡ እንዲነሳ  የተለያዩ መረጃዎችን በማሰራጨት አገሪቷ ወደ  ግጭት እንድትገባ በማድረግ በአገሪቷ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እንዲደርስ አድርጋለችም ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት አሜሪካ መገናኛ ብዙሃኖቿን ተጠቅማ በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ሐሰተኛ መረጃዎች እንዲያሰረጩ በማድረግ የስነ ልቦና ጦርነት መክፈቷን ነው ወይዘሮ አስኳል የገለጸችው።

የስነ ልቦና ጦርነቱ ሕዝቡ ከመንግስት የመነጠል ሴራ ነው፤ይህንንም መንግስትም ሕዝብም በውል መረዳታቸውንና አሁንም ይህን ሴራ ይበልጥ ሕዝቡ እንዲገነዘበው ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ትውልደ-ኢትዮጵያውያን አንዳንድ የአሜሪካ ባለስልጣናት ሽብርተኛውን ሕወሓት መደገፋቸውን ካላቆሙ በቀጣይ በተለያዩ ግዛቶች በሚደረጉ ምርጫዎች በድምጽ እንደሚቀጣቸው ተናግረዋል።

ትውልደ-ኢትዮጵያውያኑ ይህንኑ ጉዳይ ለአሜሪካ መንግስት ማሳወቃቸውንና ድምጻቸውን በመንፈግ ያላቸውን አማራጭ ለመጠቀም እንደ ስትራቴጂ ይዘው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት የሚኖሩት ዳያስፖራ አቶ ከባዱ ሙሉቀን በበኩላቸው ሕወሓት የደርግ መንግስትን ለመጣልና ስልጣን ለመያዝ ሕዝብን የመከፋፋል ስልትና የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በተደራጀ መልኩ መጠቀሙን አስታውሰዋል።

ሕወሓት ስልጣን ከያዘ በኋላም በከፍፋለህ ግዛው አስተሳሰብ የኢትዮጵያዊነትን ስሜት ለማጥፋት መስራቱን አመልክተዋል።

ቡድኑ ስልጣን ለመያዝ የተጠቀመበትን ሴራ አሁንም ለመድገም እየጣረ መሆኑንና ይህንንም ኢትዮጵያውያን መረዳታቸውን ገልጸዋል።

አሜሪካም የሕወሓትን የውሸት ትርክት ተቀብላ በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ክህደት ጆሮ ዳባ ልበስ እንዳለችው አመልክተዋል።

“የሕወሓት ቡድን ከአሜሪካ መንግስት ባለስልጣናት ጋር ያለውን ግንኙነት ተጠቅሞ መገናኛ ብዙሃኖቻቸው ላይ የእሱ ሀሳብ ብቻ እንዲንጸባረቅ እየሰራ ነው” ብለዋል አቶ ከባዱ።

የዳያስፖራው ማህበረሰብ አባላት ይህንኑ ጉዳይ በመገንዘብ የኢትዮጵያን ሕልውና ለማስጠበቅ ለሚደረገው ጥረት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

ከሰሞኑ በዋሺንግተን ዲሲ የሕልውና ዘመቻውን በመደገፍና የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት በመቃወም የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ጉዳይ እንደማይደራደርና ጣልቃ ገብነትን እንደማይቀበል በተግባር ያሳየበት እንደሆነ የዳያስፖራ ማህበር አባላቱ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም