ለአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ውጤታማነት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ገለፁ

95
አዲስ አበባ ነሀሴ 14/2010 ለአዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ውጤታማነት  ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ገለፁ። አንድ አገር ሁለንተናዊ እድገትን በማምጣት የዜጎችን ኑሮ ማሳደግ የምትችለው በሚኖራት የሰው ኃይል አቅም ነው። በሳይንስና ቴክኖሎጂ በልጽገው በአገራቸው ልማትን በማምጣት ለህዝቦቻቸው የጠቀሙ አገሮችን እንደ አብነት ደቡብ ኮሪያ፣ ቻይና፣ ሴንጋፖርን ተሞክሮ መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ አገሮች ለትምህርትና ስልጠና በሰጡት ልዩ ትኩረት የሰው ኃይል ሀብታቸውን በማልማትና እድገት በማስመዝገብ የህዝቦቻቸውን ኑሮ ማሻሻል ችለዋል። በኢትዮጵያ በ1986 ዓ.ም የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ በመቅረጽ ባለፉት ዓመታት በዘርፉ ሲሰራ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ላለፉት ሃያ ዓመታት በተግባር ላይ ያለው የትምህርት ፖሊሲ ያስገኘው ጥቅም እንዳለ ሆኖ ብዛት ላይ እንጂ የትምህርት ጥራት ላይ ክፍተቶች እንዳሉበት ስለሚተች በአብዛኛው ፍሬያማ አለመሆኑ ይነገራል። ታዲያ ይሄንን ችግር ለመፍታት በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው  የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ውይይት ተደርጎበታል። በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ምሁራን ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የትምህርትና ሥልጠና ተቋማትን በማስፋፋት የትምህርት ተደራሽነትንና ፍትሃዊነትን በማጎልበት ረገድ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል። ሆኖም ግን የተማሪዎችን የመማር ውጤት ከማሻሻል አኳያ በፖሊሲው የተቀመጠውን የመማር ውጤት በማረጋገጥ በኩል ችግሮቹ የገዘፉ መሆናቸውን ገልፀዋል። ይህም አገሪቱ የምትፈልገውን ብቁና በቂ የሰው ኃይል በማፍራት በኩል አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ በመሆኑ አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ  ችግሩን ለመፍታት አስተዋፆ የሚኖረው በመሆኑ ለውጤታማነቱ መሳካት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ገልፀዋል።   የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በሰጡት አስተያየት "አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ብዙ ነገር አሳይቷል፤ትልቁ ክፍተት አድርጎ ያስቀመጠው ጥራትን ነው፤ እኛ እንደ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የጥራትን ነገር በዋናነት የምናየው ነው። እኛ መካተት አለበት ብለን ስንመለከት በሳይንስ ትምህርቶች ላይ መሰራት እንዳለበት ብዙ ነገሮችን ያመላከተ ነው።" ብለዋል፡፡ "ፍኖተ ካርታው አገራችንን የሚጠቅም ነገር ነው፤የትምህርት ሪፎርም ስራዎች  እንደሚያስፈልጉና የዚህ ሪፎርም ስራ ዋና አላማው  ጥራቱን  ለማሻሻል በመሆኑ ከቴክኖሎጂ ጋር የሚሄድ አካሄድ ለመፍጠር በመሆኑ የፖለቲካ መሪው ድርሻ ወሳኝ በመሆኑ  እንደ ክልል አመራሮች የየራሳችን ድርሻ በጣም አስፈላጊ ነው" ያሉት የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት አስተያየት ሰጪዎቹ በአገሪቱ የትምህርት ሥልጠና ችግሮችና ተግዳሮቶች የተለዩ በመሆኑ ችግሮቹን ለመፍታት ጥናትን መሰረት ያደረገው የማሻሻያ ሥራዎችን ለመስራት አዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም