አርሶ አደሮች የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል በመሰብሰብ የሕልውና ዘመቻውን እያገዙ ነው

71

አዲስ አበባ ህዳር 3/2014 /ኢዜአ/ የሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር አርሶ አደሮች የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል በመሰብሰብ የሕልውና ዘመቻውን በማገዝ ተግባር ተሰማርተዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራ ክልል በወረራቸው አካባቢዎች እያደረሰ ያለውን ኢ-ሠብዓዊ ድርጊት ለማስቆምና ቡድኑን እስከወዲያኛው ለማጥፋት ሕዝቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ነው።

ሸዋሮቢት ላይ በሰብል ስብሰባ የተሰማሩ   አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንዳስረዱት የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ የሕልውና ዘመቻውን እያገዙ ነው ።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ ያለው የሽብር ቡድኑ ህወሓት በአማራ ክልል በወረራቸው አካባቢዎች የአርሶ አደሮችን ሰብል እየዘረፈና እያወደመ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የሽብር ቡድኑ የደቀነውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ አቅማቸው በፈቀደ ሁሉ እየተጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የአካባቢው አርሶ አደሮች ወደ ግንባር  በመዝመት፣ አካባቢያቸውን ከሰርጎ ገቦች በመጠበቅና የጸጥታ ኃይሉን በመደገፍ ተግባራት እየተሳተፉ መሆኑንም አስረድተዋል።

አገር ለማፍረስ ከቤታችን ድረስ ሰተት ብሎ የመጣውን የሽብር ቡድን ለመደምሰስ በቅድሚያ ግንባር የዘመቱ የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል እየሰበሰብን ነው ብለዋል።

"ዘማቾች ከሌሉ እኛ የለንም" ያሉት አርሶ አደሮቹ ለዘማች ቤተሰቦች የሚያስፈልገውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።

ይህም ብቻ ሳይሆን የሽብር ቡድኑ እያለ ኢትዮጵያ ሠላም ስለማታገኝ ሰብላችንን ከሰበሰብን በኋላ "ወደ ግንባር እንዘምታለን" ሲሉ ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑን መውጫና መግቢያ በመዝጋት የአካባቢያቸውን ሠላም እያስጠበቁ መሆኑንም ገልጸዋል።

ወቅቱ የሰብል መሰብሰቢያ በመሆኑ የደረሱ ሰብሎችን በጋራ በመሰብሰብ 'የሠላማችን ጸር የሆነውን ጠላት በጋራ እየተከታተልን ነው' ብለዋል አርሶ አደሮቹ።

የሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አቤኔዘር ከበደ፤ የሰብል መሰብሰብ ስራው የህልውና ዘመቻው አካል መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ለህልውና ዘመቻው ግንባር የዘመቱ አርሶ አደሮችን ሰብል ቅድሚያ በመስጠት እንደተሰበሰበላቸው ተናግረዋል።

ሕዝቡ የደረሱ ሰብሎችን ከመሰብሰብ ጎን ለጎን የጸጥታ ሃይሉን እንዲደግፍ፣ እንዲዘምትና አካባቢውን ከሰርጎ ገቦች እንዲጠብቅ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም