በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለተፈናቃሉ ወገኖች ግምቱ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ድጋፍ አደረጉ

72

ህዳር 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአሽባሪው ህውሃት ወረራ ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ወገኖች ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረጉ።

ኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ የቦርድ አባል አቶ ከበደ ሃይለማሪያም ዛሬ በተካሄደው የድጋፍ ርክክብ ላይ እንዳሉት፤ በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጰያውያን የወገናቸውን ስቃይ ለመጋራት በማሰብ በበይነ መረብ መርሃ ግብር ከተቆርቋሪ ወገኖች ሃብት ማሰባሰብ ተችሏል።

በዚህም  ''በሸዋ ሰላምና ልማት ማህበር'' በኩል ለተፈናቃዮች ድጋፉ እንዲደርስ መመቻቸቱን አስረድተዋል።

የተፈናቃዮች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ቀጣይ ተጨማሪ ድጋፍ ለማሰባሰብ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የሸዋ ሰላምና ልማት ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው በበኩላቸው፤ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ወረራ በመፈጸም ላፈናቀላቸው የደቡብና ሰሜን ወሎ ዞኖች ወገኖችን ምላሽ ለመስጠት የመንግስት አቅም ብቻ በቂ አለመሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የልማት ማህበሩ ''ለወገን ደራሽ ወገን ነው'' በማለት በውጭ ለሚኖሩ ደጋፊዎቹ ባቀረበው የድጋፍ ጥያቄ መሰረት 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ድጋፍ መገኘቱን አስረድተዋል።

በዚህም በደብረ ብርሃን ከተማ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ከ10 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ወገኖች 200 ኩንታል ሩዝ፣ አንድ ሺህ ብርድ ልብስ፣ 1 ሺህ 200 መመገቢያ ሳህኖች፣ 2 ሺህ ሊትር ዘይትና ሌሎችም ቁሶች ድጋፍ ተደርጓል።

በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ወገኖች የችግሩን ስፋት  በመረዳት የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ፕሮፌሰር ሲሳይ ጥሪ አቅርበዋል።

በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የበጀትና የፋይናስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፀጋየ በየነ እንዳሉት፤ የሸዋ ሰላምና ልማት ማህበር ለተፈናቃዮች ከአጋሮቹ አሰባስቦ ድጋፍ ሲያደርግ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

የተፈናቃዮች ቁጥር  እየጨመረ በመምጣቱ  ሌሎች አጋር አካላትም በምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።አመልክተዋል።

ለተፈናቀሉ ወገኖች በካናዳ ከሚገኝ ''ወገን ለወገን መረዳጃ ማህበር" 450 ሺህ ብር ድጋፍ መደረጉን የማህበሩ ተወካይ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ዳምጠው ተሰማ ገልጸዋል።

በተገኘው ድጋፍም 80 ኩንታል የምግብ እህልና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች ተገዝተው መከፋፈላቸውን ጠቅሰዋል።

የተፈናቀሉ ወገኖች እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ ጊዜያዊ ችግሮቻቸውን እንደሚፈታ ተናግረዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም