በሶማሊ ክልል የተዘረፉ ንብረቶችን በማስመለስ ሂደት የእምነት አባቶችና የጎሳ መሪዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ

70
ጅግጅጋ ነሃሴ 14/2010 በሶማሊ ክልል ተከስቶ የነበረውን ሁከት በማስወገድ እና የተዘርፉ ንብረቶችን በማስመለስ ሂደት የእምነት አባቶችና የጎሳ መሪዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ፡፡ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የክልሉን ሰላም ለማረጋጋት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከህብረተሰቡ ጋር ሲያከናውን የቆየውን ተግባር አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ የደቡብ ምስራቅ ዕዝ ኢንዶክትሬሽን ዳይሬክቶሪት ዳይሬክተር ኮሌኔል ተክላይ ገብረ እግዚአብሔር በመግለጫቸው እንዳሉት በክልሉ ተፈጥሮ የነበረው ሁከትና ግርግር ህብረተሰቡን የሚወክል ባለመሆኑ በማህበረሰቡ ዘንድ ቁጣ ፈጥሯል፡፡ ’’ሁከቱ ከሶማሊ ባህልም ሆነ ሃይማኖት አንፃር ሊደረግ የማይችል በመሆኑ ህብረተሰቡ ውስጥ ሰፊ ቁጣ ፈጥሯል’’ ብለዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶችና የጎሳ መሪዎች በእምነት ተቋማት ህዝቡን ስለሰላም ጠቀሜታ በማስተማር እና የተዘረፉ ንብረቶች እንዲመለሱ በማድረግ አካባቢው በፍጥነት ወደ ነበረበት መረጋጋት እንዲመለስ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን በመሆን ከፍተኛ ድርሻ መወጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ ከህብረተሰቡ መሪዎች ጋር በመሆን የክልሉን ሰላም በዘላቂነት እንዲረጋገጥ ከመስራት ባሻገር  የተቋቋሙ የተለያዩ ኮሚቴዎች በርካታ የተዘረፉ ንብረቶች እንዲመለስ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ ከኮሚቴው ጋር በመሆንም ባለፉት ሶስት ቀናት ውስጥም 200 ባጃጆችና ሌሎች ተሽከርካሪዎችን ለባለንብረቶቹ ማስረከቡን ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም ሶፋ፣ ማቀዝቀዣ፣ ልብስ ማጠቢያ ማሽን እና ሌሎች የቤት ወስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች ማስመለሱን ገልፀዋል፡፡ የክልሉ ባህላዊ መሪዎች እና የሃይማኖት አባቶች በክልሉ ተከስቶ የነበረውን ሁከት ለማስወገድ እና የተዘርፉ ንብረቶች እንዲመለሱ ላበረከቱት አስተዋፅኦ አመስግነዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም