በአማራ ክልል የክረምት ጎርፍ አደጋን ለመከላከል ከወዲሁ እየተሰራ ነው

82
ባህር ዳር ግንቦት 9/2010 በአማራ ክልል በክረምት ወቅት ሊደርስ የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች ከወዲሁ እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽፈት ቤት አስታወቀ። የጽፈት ቤቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ዳይሬክተር አቶ ጀንበሩ ደሴ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ 32 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸው በጥናት ተረጋግጧል። በአሁኑ ወቅት የጎርፍ አደጋውን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ያሉት በሰባት ዞኖች በሚገኙ 16 ወረዳዎች ውስጥ መሆኑን ገልጸው ለእዚህም 15 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን አስታውቀዋል። በክልሉ ከተለዩ የጎርፍ ተጋላጭ ቦታዎች መካከል ሰሜን ሸዋ፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ደቡብና ሰሜን ወሎ፣ ደቡብና ሰሜን ጎንደር እንዲሁም ምዕራብ ጎጃም ዞኖች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። አቶ ጀንበሩ እንዳሉት የሚደርሰውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከልና ለመቀነስ እንዲቻል በጥናት በተለዩ አካባቢዎች አዳዲስ የጎርፍ ማፋሰሻ ቦይ የመስራትና የነበሩትን የመጠገን ሥራ እየተከናወነ ነው። ለዚህም በሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋ ሮቢት፣ አጣየ፣ ማጀቴና መኮይ ከተሞች እንዲሁም ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ እየተሰሩ ያሉትን አዳዲስ የጎርፍ መከላከያ ቦዮችና የነበሩትን የመጠገን ሥራ በማሳያነት ጠቅሰዋል። ከዚህ በተጨማሪ ግድቦች ሞልተው ወደ ህብረተሰቡ እንዳይፈሱ የዳርቻቸውን ቁመት የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ነው ያስረዱት። ወደ ጣና ሐይቅ በሚፈሱ የርብ፣ የመገጭና የጉማራ ወንዞች መሙላትና መፍሰስ ጋር በተያያዘ  በደራ፣ ፎገራ፣ ሊሞከምከም ወረዳዎችና ወረታ ከተማ አስተዳደር ሊደርስ የሚችለውን የጎርፍ መጥለቅለቅ ለመታደግ የግድብና የተፋሰስ ልማት ሥራዎቹ እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል። ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ደዋጨፋ፣ አርጡማፉርሲና ጅሌ ጥሙጋ ወረዳዎች ሊደርስ የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከልም ተመሳሳይ የግንባታ ሥራዎች እንደሚከናውንባቸውም አቶ ጀንበሩ አመልክተዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ የቅድመ መከላከል ሥራ ከመስራት በተጨማሪ በጎርፍ ምክንያት ለሚደርስ መፈናቀል በጣና ሐይቅ ዙሪያ ፎገራ፣ ደራና ደንቢያ ወረዳዎች ስምንት ጊዜአዊ የመጠለያ ቦታዎች ቀደም ሲል ተግንብተው ተዘጋጅተዋል። በክረምት ወቅት የአሰሳና ቅኝት ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችሉ ሦስት ጀልባዎች በፕሮጀክት እንዲገዙ መደረጉንም አስታውቀዋል። መንግስት በጀት መድቦ ከሚያከናውናቸው የጎርፍ መከላከል ሥራዎች በተጨማሪ በየአካባቢው ማህበረሰቡ የአፈርና ውሃ ጥበቃና ጎርፍ የመከላከል ሥራዎችን እንዲሰራ አቅጣጫ ተቀምጦ ወደተግባር መገባቱን አቶ ጀንበር ገልጸዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም