በመጪዎቹ ሦስት ወራት የምግብ ዋጋ ቅናሽ እንደሚያሳይ ተተነበየ

76

ህዳር 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሚቀጥሉት ሦስት ወራት የምግብ ዋጋ ቅናሽ እንደሚያሳይ መተንበዩን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው በየወሩ በሚያወጣው  የዋጋ ግሽበት መረጃ መሰረት የጥቅምት ወርንም ይፋ አድርጓል።

 በአጠቃላይ ባለፈው ወር 34 ነጥብ 8 በመቶ የደረሰው የዋጋ ግሽበት በጥቅምት ወር ወደ 34 ነጥብ 2 በመቶ ዝቅ ብሏል ሲል ኤጀንሲው ገልጿል።

በያዝነው ወር በእህሎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ በመጠኑ የተረጋጋ ሲሆን ሩዝ፣ ጤፍና ስንዴ አነስተኛ የዋጋ ቅናሽ አሳይተዋል ነው ያለው፡፡

ሥጋ፣ ወተት፣ አይብና ዕንቁላል፣ ቅመማ ቅመም (በዋናነት ጨውና በርበሬ) መጠነኛ ቅናሽ ማሳየታቸውንም ኤጀንሲው አስታውቋል።

የጥቅምት 2014 ዓ.ም ወርሀዊ የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው መስከረም ወር ጋር ሲነጻጸር በ1 ነጥብ 3 በመቶ የቀነሰ ሲሆን በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት መረጋገቱን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ገልጿል።

የረዥም ጊዜ ወቅታዊ የዋጋ ግሽበት አዝማሚያ እንደሚያሳየው ከመኸር ወቅት የግብርና ምርት ጋር በተያያዘ በሚቀጥሉት ሶስት ወራት የምግብ ዋጋ ይቀንሳል ተብሎ ይገመታል ሲልም አስታውቋል።

በአገር ውስጥ የሚዘጋጀው ዘይትና ቅቤ ዋጋ ትንሽ ቀንሷል የቡና የዋጋም ጭማሪ አሳይቷል ነው የተባለው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የበቆሎ ዋጋ  በመጠኑ መጨመሩ የተገለጸ ሲሆን  ከውጭ የሚገባው የምግብ ዘይት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር የዋጋ ጭማሬ አሳይቷል ተብሏል።

ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት የጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም የ25 ነጥብ 2 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተነግሯል።

በሌላ በኩል የዋጋ ግሽበቱ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ34 ነጥብ 2 ከመቶ ከፍ ያለ ሲሆን የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ በ40 ነጥብ 7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ሲል ገልጿል፡፡

ከምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍ እንዲል ካደረጉት ዋና ምክንያቶች ውስጥ በተለይም በአልኮልና ትምባሆ፣ ልብስና ጫማ፣ አነቃቂዎች (ጫት)፣ የቤት እንክብካቤና ኢነርጂ (ማገዶና ከሰል)፣ የቤት መስሪያ እቃዎች (የቤት ኪራይ፣ ሲሚንቶ፣ የቤት ኪዳን ቆርቆሮ)፣ የቤት ዕቃዎችና የቤት ማስጌጫዎች)፣ ህክምና እና ጌጣጌጥ (ወርቅ) ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ነው ሲል አስታውቋል፡፡

በክልል ደረጃ በጥቅምት ወር በአዲስ አበባ ከተማ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ከሌሎች ክልሎች ጋር ሲነጻጸር የዋጋ መረጋጋት ሁኔታ አሳይተዋል፡፡

በአጠቃላይ ከባለፈው ወር 34 ነጥብ 8 በመቶ የደረሰው የዋጋ ግሽበት በጥቅምት 2014 ዓመታዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ወደ 34 ነጥብ 2 በመቶ ዝቅ ብሏል ሲል ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መረጃ ገልጿል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም