የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ134 ሺህ የካናዳ ዶላር በላይ አሰባሰበ

87

ህዳር 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ የሚውል ከ134 ሺህ የካናዳ ዶላር በላይ ማሰባሰቡን አስታወቀ።

የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ ከቀናት በፊት "ለአስቸኳይ የእናት አገር ጥሪ ምላሽ" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው የበይነ መረብ መርሃ ግብር በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ የሚውል 134 ሺህ 213 ዶላር ማሰባሰቡን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ገንዘቡ የተሰባሰበው በመርሃ ግብሩ ላይ ከተገኙ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች፣ በሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ዳያስፖራዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆች መሰብሰቡን አመልክቷል።

ከተሰበሰበው የገንዘብ መጠን በተጨማሪ በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉ ሰዎች ገንዘብ ለመስጠት ቃል መግባታቸውንና ድጋፉ እንደሚቀጥልም ገልጿል።

የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ ባለፈው አንድ ዓመት ለሰብአዊ ድጋፍ የሚውል ከ142 ሚሊዮን ብር በላይ በገንዘብና በአይነት በማሰባሰብ መርዳቱንም ገልጿል።

የድርጅቱ አባላት በጦርነቱ ሳቢያ ከቀያቸው ለተፈናቀሉና ንብረታቸው የወደመባቸውን መልሶ ማቋቋም የሚደረገውን እንቅስቃሴ በገንዘብ፣ በቁሳቁስና ሙያዊ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉም አስታውቋል።

በቀጣይ የሰብአዊ ድጋፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮችን በቶሮንቶና በኦቶዋ እንደሚያካሄድም ጠቁሟል።

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብና የምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያለውን ጣልቃ ገብነት፣ የዲፕሎማሲ ጫና እና የሐሰተኛ መረጃ ዘመቻቸውን በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እንደሚመክቱም ነው መግለጫው ያመለከተው።

መንግስት የጀመረውን የሕልውና ዘመቻ አጠናክሮ እንዲቀጥልና የአሸባሪው ሕወሓት አጀንዳ ተሸካሚዎች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርቧል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም