ከአሸባሪው ሕወሓትና ሸኔ ጋር ግንኙነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር

86

አዳማ ጥቅምት 1/2014 (ኢዜአ) በምስራቅ ሸዋ ዞን ከአሸባሪው ሕወሓትና ሸኔ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የዞኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈፃሚ ኮሚቴ ገለፀ።

የምስራቅ ሸዋ ዞን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አባቡ ዋቆ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ በሕግ ቁጥጥር ስር የዋሉት ሀገርን ለማፍረስ ከተሰለፉ ኃይሎች ጋር ቁርኝት እንዳላቸው ተጠርጥረው ነው።

በሕግ ቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች  ከአሸባሪዎቹ  ህወሓትና ሸኔ ጋር ቀጥታኛ ግንኙነት እንዳላቸው፣ በገንዝብና በቁሳቁስ የሚደግፉና በመረጃ አብረው ተባብረው እንደሚሰሩ የተጠረጠሩ ናቸው።

በተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ቤት በተደረገው ፍተሻ ለአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ የጥፋት  ዓላማ ማስፈፀሚያ ያዘጋጁት ሰነዶች፣ የእጅ ቦንቦችንና ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሳሪያ ጥይቶች ተገኝተዋል።

ከዚህም ባሻገር ሰሞኑን  የአቅጣጫ አመላካች ኮምፓስ የያዙ አሸባሪው ህወሓት ሰርጎ ገቦች በመተሓራ ከተማ፣ በሉሜና በፈንታሌ በኩል ወደ ዞኑ ሲገቡ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

የተያዙ የአሸባሪው ህወሓት ሰርጎ ገቦች አዳማ ከተማን ጨምሮ በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች ከአሸባሪው ሸኔ ጋር በትብብር ለመስራ የሚያስቸላቸው በእቅድ የተደገፈ ሰነድ መገኘቱንም አስረድተዋል።

በተጨማሪም የመገናኛ መሳሪያዎችና የተለያዩ የጦር ማሳሪያዎች ከመሰል ጥይቶች ጋር መያዛቸውንም ተናግረዋል።

ከሽብር ቡድኖቹ ጋር ግንኙነት እንዳለቸው በተጠረጡ ግለሰቦች መኖሪያ ቤት ላይ በተደረገ ፍተሻ ለሽብር ተግባር የተዘጋጁ ታርጋና የባለቤትነት ማረጋገጫ ልብሬ የሌላቸው የሞተር ሳይክሎችም ተይዘዋል ብለዋል።

የመንግስትና የህዝብ የልማት ተቋማት ለማውደምና አመራሮችን ለመግደል በሰነድ የተዘጋጀ እቅድ በአሸባሪው ህወሓት ተላላኪዎች እጅ መገኘቱንም ተናግረዋል።

ህዝቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመተባበር አካባቢውን ነቅቶ እየጠበቀ ነው ያሉት የኮሚቴው ሰብሳቢ "ዞኑ  ከአፋርና አማራ ክልሎች ጋር የሚዋሰን በመሆኑ የአጎራባች ወረዳዎችን ፀጥታ ለማጠናከር በትብብር እየሰራን ነው" ብለዋል።

በተለይ ሰርጎ ገቦችን ከመቆጣጠር ባለፈ የአሸባሪውን ሸኔ በማፅዳትና እንቅስቃሴውን ለማምከን እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የዞኑ ሕዝብ ተደራጅቶ አካባቢውን ከሽብር ቡድኑ ሰርጎ ገቦች እንቅስቃሴ  መጠበቅና ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ቀን ከሌሊት በትብብር በመስራት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ አባቡ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም