ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ ያለውን የአሸባሪው ህወሃት እኩይ ሴራ ለማክሸፍ ጠንክረን እንሰራለን

54

ጋምቤላ ፤ ህዳር 1/2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ ያለውን አሸባሪው የህወሓት ቡድንና የተላላኪዎቹን እኩይ ሴራ ለማክሸፍ ጠንክረው በመስራት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የጋምቤላ ክልል የሀገር ሽማግሌዎችና ተዋቂ ግለሰቦች ገለጹ።

ከክልል የተወጣጡ  የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የአመራር አካላት በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ በጋምቤላ ከተማ ሲያካሄዱ የቆዩት ውይይት የአቋም መግለጫ በማውጣት አጠናቀዋል።

ተሳታፊዎቹ በመግለጫቸው፤ አሸባሪው የህወሓት ቡድንና ተላላኪዎቹ በንጹሐን ዜጎች ላይ እያደረሱ ያሉትን  ኢ-ሰብአዊ ድርጊትና የመሰረተ ልማት አውታሮች  ጥፋት ለማስቆም ሁሉን አቀፍ ድጋፍና ርብርብ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

የኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ ያቃታቸው አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ የምዕራባውያን ሀገራት ጊዜው ያለፈበትን የመጨዋቻ ካርድ በመያዝ በአሻንጉሊቶቻቸው አማካኝነት እየፈጠሩት ያለውን ጫና አጥብቀው እንደሚቃወሙም አስታውቀዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ባለፉት 27 ዓመታት በጋምቤላ ክልል የፈጸመው የዘር ማጥፋትና ዘረፋዎች ሳያንሰው አሁንም ከተላላኪዎቹ ጋር በመሆን የቀድሞውን ድርጊቱ ለመድገም የሚያደርገው እንቅስቃሴ አምረው እንደሚታገሉም ገልጸዋል።

በየግንባሩ እየተዋደቀ ካለው የመከላከያ፣ የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት ጎን በመሰለፍ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመወጣትም ቃል ገብተዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው፤ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በተንኮል ተወልዶ በውሸት ያደገ የኢትዮጵያና ህዝቦቿ ቀንደኛ ጠላት ነው ያሉት።  

አሸባሪው ህወሃት  ባለፉት አራት አስራት ዓመታት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲሰራ የቆየ አረመኔ ቡድን መሆኑን አውስተዋል።

ቡድኑ በክልሉ ባለፉት 27 ዓመታት በኑዌር፣ አኝዋሃና ማጀንግ ላይ ብሔር ተኮር ጥቃትና ዘረፋ ሲፈጽም የነበረ አሸባሪ ቡድን መሆኑንም አስታውሰዋል።

የጥፋት ቡድኑ እየቃጠ ያለው ሀገር የማፈረስ እኩይ ተግባር ለመቀልበስ ሁሉም የህልውና ዘመቻው አካል ሊሆን እንደሚገባ ነው ርዕሰ መስተዳደሩ ያሳሰቡት።

ለሁለት ቀናት በተካሄደው የውይይት መድረክ  ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ ከ220 በላይ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና አመራሮች ተሳትፈዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም