ግብር በወቅቱ እንዳንከፍል አቅማችንን ያላገናዘበ የገቢ ግመታና የደረጃ ለውጥ ችግር ፈጥሮብናል - የአርባምንጭ ነጋዴዎች

72
አርባምንጭ ነሀሴ 14/2010 አቅማቸውን ያላገናዘበ የገቢ ግመታና የደረጃ ለውጥ ግብር በወቅቱ ለመክፈል ችግር እንደፈጠረባቸው አስተያየታቸውን ለኢዜአ  የሰጡ የአርባ ምንጭ ከተማ ነጋዴዎች ገለፁ፡፡ አስተያየታቸውን ከሰጡ የደረጃ 'ሐ' ነጋዴዎች መካከል የአትክልትና ፍራፍሬ ነጋዴዋ ወይዘሮ አስቴር ዲቃሞ ግብር ለአገር ልማት ያለው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ይሁን እንጂ  የተጠየቁት ግብር ከአቅም በላይ በመሆኑ ለመክፈል መቸገራቸውን ጠቅሰዋል ፡፡ እስከ 2008 ዓ.ም በየዓመቱ 1ሺህ 800 ብር እየከፈሉ ቢቆዩም ባለፈው ዓመት በተደረገው የገቢ ግመታ 15 ሺህ 820 ብር እንዲከፍሉ መወሰኑን አስረድተዋል ፡፡ እንዲሻሻልላቸው ያቀረቡት ቅሬታ ተቀባይነት ባለማግኘቱ የተወሰነባቸውን መክፈላቸውን ገልፀው ዘንድሮ ግን ይህንን ማድረግ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ በቤት ዕቃዎች ንግድ ሥራ የደረጃ 'ለ' ነጋዴ አቶ ወንድወሰን በየኔ በበኩላቸው ''የባለስልጣኑ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ያለምንም ተጨባጭ መረጃ ከደረጃ ለ ወደ ሀ በማሳደጉ ያለፈውን ዓመት ግብር ተገድጄ ከፍያለው'' ብለዋል፡፡ ''ዘንድሮ ስህተታቸውን አርመው ከደረጃ ሀ ወደ ለ ቢመልሱኝም የተጣለብኝ ግብር አቅሜን ያላገናዘበ ነው'' ብለዋል ፡፡ የደረጃ ለ እና ሀ ግብር ከፋዮች ትልቁ ችግር አዲስ አበባ ላይ የሚገኙ አከፋፋይ ድርጅቶች ደረሰኝ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸው እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡ ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታ ቢሆንም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር አለመወያየቱ ሌላኛው ችግር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ''መጋዘን የሌለኝ መሆኑ እየታወቀ 'ከደረጃ ለ ወደ ሀ መግባት ሲገባህ ሁለት ወር ዘግይተሃል' በሚል'' 18 ሺህ ብር ቀጥተውኛል ያሉት ደግሞ የደረጃ ሀ ነጋዴ አቶ ፃባላ ፀጋዬ ናቸው ፡፡ ''በግዴታ የደረጃ ለውጥ ከመደረጉም በላይ እኔ በማቀርበው መረጃ ሳይሆን መስሪያ ቤቱ በሚያስተላልፈው የግብር ውሳኔ በመሆኑ ሥራዬን በአግባቡ መሥራት አልቻልኩም'' ብለዋል ፡፡ የአርባ ምንጭ ከተማ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አየለ ተፈራ በበኩላቸው  ከደረጃ ለውጥ እና ገቢ ግመታ ጋር በተያያዘ ነጋዴዎች ያነሱት ጥያቄ ተገቢ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የግብር ሂደቱ በጥናትና በውይይት ያልተደገፈ መሆኑ የግብር ወቅቱ ሲደርስ አብዛኛውን ነጋዴ ማስቆጣቱን ተናግረዋል፡፡ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲፈቱ ለአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደርና ገቢዎች ቢያሳውቁም እስካሁን  ምላሽ እንዳልተሰጠ ገልፀዋል፡፡ በአርባ ምንጭ ከተማ ገቢዎች ባለስልጣን ጽህፈት ቤት የገቢ አሰባሰብና ክትትል ዋና ሥራ ሂደት ባለቤት አቶ አንዷለም አስሌ በበኩላቸው በከተማው ከ8 ሺህ በላይ የደረጃ 'ሀ' ፣ ለ እና 'ሐ' ግብር ከፋዮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ሆኖም ግን ከደረጃ 'ሐ' 17 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ብቻ መሰብሰቡን ገልፀው አፈፃፀሙ ከእቅዱ በግማሽ የቀነሰው የግብር ግመታው ፍትሃዊ አይደለም በሚል ሰበብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ''የገቢ ግመታውም ሆነ የደረጃ ለውጡ የነጋዴውን የንግድ እንቅስቃሴ ያገናዘበ በመሆኑ ሊሻሻል አይችልም'' ነው ያሉት ፡፡ በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ባሉት ነጋዴዎች መካከል በባለሙያዎቻችን ስህተት የግብር እና የደረጃ ልዩነት ቢኖርም ቅሬታቸውን በመመልከት ምላሽ እየሰጠን መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ማዕከላዊ ገበያ ላይ የሚገኙ ጅምላ ሻጮች ደረሰኝ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተከትሎ ለሚፈጠረው ችግር ዘላቂ መፍትሄ እንዲገኝ የፌደራል ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን ዋና መስሪያ ቤት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ከግብር ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ ችግሮች ዙሪያ ለመመካከር ከንግድ ማህበረሰቡ ጋር የውይይት መድረክ እንደሚኖር ጠቁመዋል ፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም