ተማሪዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎች ሳይረበሹ ተረጋግተው ፈተናቸውን መውሰድ አለባቸው

72

አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2014(ኢዜአ)ተፈታኝ ተማሪዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎች ሳይረበሹ ተረጋግተው ፈተናቸውን መውሰድ እንዳለባቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የትምህርት ቤት አመራሮች ገለጹ፡፡

ኢዜአ በመዲናዋ ተዘዋውሮ ቅኝት ባደረገባቸው ትምህርት ቤቶች የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሰላማዊ በሆነ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

የትምህርት ቤቶቹ ርዕሰ መምህራን ተፈታኝ ተማሪዎች በሀሰተኛ መረጃዎች ሳይረበሹ ተረጋግተው ፈተናቸውን መውሰድ እንዳለባቸው ነው የተናገሩት፡፡

የእንጦጦ አምባ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ መሀመድ ሀሰን ፈተናውን ለሚወስዱ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ቅዳሜ እለት ስለፈተናው አጠቃላይ ሁኔታ ገለጻ እንደተደረገላቸው ተናግረዋል፡፡

ተማሪዎቹ በገለጻው መሰረት ዝግጅት አድርገው ፈተናውን እየወሰዱ ስለመሆኑ ተናግረው፤ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች ሳይረበሹ ተረጋግተው ፈተናቸውን መውሰድ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

የመድኃኒአለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ደረጄ ከበደ በበኩላቸው ተፈታኝ ተማሪዎች  የኮሮና ቫይረስ ጥንቃቄ መመሪያን በመተግበር ፈተናውን እየወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በፈተና ጣቢያዎች አስፈላጊው የደህንነት ፍተሻ እየተተገበረ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

ከወላጆች፣ ትምህርት ቤቱ ማህበረሰብና ከፀጥታ አካላት የተውጣጡ ሰባት አባላት ያሉት ኮማንድ ፖስት መዋቀሩን አስረድተው፤ የኮማንድ ፖስቱ አባላት ፈተናው ሰላማዊ በሆነ አግባብ እንዲካሄድ የማስተባበር ስራ እያከናውኑ መሆኑን አንስተዋል፡፡  

እስካሁን ባለው ሁኔታም ከአንዳንድ ተማሪዎች መዘግየት ውጪ ያጋጠመ ችግር አለመኖሩንም ገልፀዋል።

የመድኃኒአለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፈተና ጣቢያ አስተባባሪ አቶ አበባው ፀጋዬ ከኮማንድ ፖስት አባላቱ ጋር በመቀናጀት ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የእንጦጦ አምባ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የፈተና ጣቢያ ኃላፊ አንዷለም ተስፋዬ በበኩላቸው ተማሪዎች ለፈተናው የተሰጠውን ሰዓት በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ለፈተናው ሂደት ሰላማዊነት በትኩረት እየሰሩ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም