የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በሰኔ 16ቱ የቦንብ ፍንዳታ ሁለት ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

60
አዲስ አበባ ነሀሴ 14/2010 የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከሰኔ 16 የቦንብ ጥቃት ጋር በተያያዘ ቦንቡን በማፈንዳት እና የፈነዳውን ቦንብ በማቀበል በተጠረጠሩት ሁለት ግለሰቦች ላይ ተጨማሪ ምርመራ ለማካሄድ ፖሊስ የጠየቀውን የሰባት ቀን ጊዜ ቀጠሮ ፈቀደ። በቁጥጥር ሥር የሚገኙት ጥላሁን ጌታቸውና ብርሀኑ ጃፋር የተባሉ ግለሰቦችን ጉዳይ ለማየት ዛሬ ለተሰየመው ችሎት የሰውና የሰነድ ማስረጃ ለማሰባሰብ በሚል ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ ጊዜ 14 ቀን ቢሆንም ፍርድ ቤቱ የተፈቀደው ግን ሰባት ቀን ነው። ከሰኔ 12 እስከ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ባሉው ጊዜ ውስጥ ተጠርጣሪዎች ያደረጉትን የስልክ ልውውጥ የተመለከተ መረጃ፤ ከኢትዮ-ቴሌኮምና ከብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ለመቀበልና ተያያዥ የምርመራ ስራዎችን ለማከናወንም ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ፖሊስ ለችሎቱ ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል። ከፍንዳታው ተጎጂዎች በኩል እስካሁን የደረሰው የ44ቱ ማስረጃ መሆኑን የጠቀሰው ፖሊስ  ክሱን ለመመስረት የሌሎች ተጎጂዎችን የህክምና ማስረጃ ከሆስፒታሎች ለመቀበል ጊዜ እንደሚያስፈልገውም ገልጿል። ''ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው የተጠየቀው ጊዜ በዝቷል፤ በዋስ ወይም በነፃ ልንለቀቅ ይገባል'' ብለዋል፡፡ ቦንብ በማፈንዳት ድርጊት የተጠረጠረው ጥላሁን ጌታቸው "በሰኔ 16ቱ ሰልፍ እንደ ማንኛውም ተሳታፊ በደረሰብኝ የቦንብ አደጋ ተገቢውን ህክምና እያገኘሁ አይደለም፣ ማረሚያ ቤትም ጉዳት እያደረሰብኝ ነው" ሲል ቅሬታውን አቅርቧል፡፡ ፖሊስ በበኩሉ በህክምናም ሆነ በአያያዝ በኩል ምንም ዓይነት ጉድለት አለመኖሩን በመግለጽ የቀረበበትን ቅሬታ አስተባብሏል፤ ''የቀረበውን ቅሬታ መሰረት በማድረግ በማንኛውም መልኩ በገለልተኛ አካል ማጣራት ይቻላል'' ብሏል። ግራ ቀኙን የመረመረው ችሎቱ የተጠርጣሪዎችን የዋስትናና በነጻ የመሰናበት ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለፖሊስ የሰባት ቀናት ቀነ ቀጠሮ ፈቅዷል። ጥላሁን ጌታቸው የተባለው ተጠርጣሪ የህክምና አገለግሎት እንዲያገኝ ያሳሰበው ችሎቱ ጉዳዩን ለማየት ለነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም