ኢትዮጵያን ከጠላት መጠበቅና ሉዓላዊነቷን ማስከበር ከአባቶች የወረስነው ባህል ነው---የጋሞ ዞን ነዋሪዎች

82

አርባ ምንጭ (ኢዜአ) ጥቅምት 28/2014 ኢትዮጵያን ከጠላት መጠበቅና ሉዓላዊነቷን ማስከበር ከጀግኖች አባቶቻችን የወረስነው ባህል በመሆኑ መቼም ቢሆን የሀገራችንን ሉዓላዊነት አናስደፍርም ሲሉ የጋሞ ዞን ነዋሪዎች አረጋገጡ፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍና አሸባሪዎቹን ህወሓትና ሸኔን የሚያወግዝ ሕዝባዊ ሰልፍ ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል፡፡

ሕዝባዊ ሰልፍ የተሳተፉት የጋሞ ዞን ነዋሪዎች በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኢትዮጵያን ከጠላት መጠበቅና ሉዓላዊነቷን ማስከበር ከጀግኖች አባቶቻቸው ወረሱት  ባህል በመሆኑ መቼም ቢሆን የሀገራቸውን ሉዓላዊነት አያስደፍሩም።

ከሰልፈኞቹ መካከል የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ አቶ ታመነ ተስፋዬ በሰጡት አስተያየት አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም እንደሚገባ ሳያፍር መናገሩ የአረመኔነቱን ጥግ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

"አሸባሪው በዜጎች ላይ እልቂት በመፈጸም፣ ንብረታቸውን በመዝረፍና በማውደም በሀገራችን ታሪክ የማይረሳው ጠባሳ ፈጽሟል፡፡"

ኢትዮጵያን ከጠላት መጠበቅና ማስከበር ከጀግኖች አባቶቻችን የወረስነው ባህላችን ነው" ያሉት አቶ ታመነ፣" መቼም ቢሆን የሀገራቸውን ሉዓላዊነት አናስደፈርም" ብለዋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አባላትን በድንገት በማጥቃት አረመኔአዊ ድርጊት የፈጸመውን አሸባሪውን ህወሓት  ለመደምሰስ የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ወጣት ምህረት ንጉሴ በበኩሏ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የነፃነት ቀንዲልና ክብሯን ያላስደፈረች ታላቅ ሀገር መሆኗን ገልጻለች፡፡

ይህን ነፃነቷንና ክብሯን እንዳለ ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ የእዚህ ትውልድ ሀላፊነት መሆኑን ገልጻ፣ "ሀገሯን ለመበተን ቆርጦ የተነሳውን ህወሓት በመፋለም የሀገሬን ክብር አስቀጥላሉ" ብላለች።       

የውጭ መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ገጽታ ለማጠልሸት ያልተጋባ ተግባር እየፈጸሙ በመሆናቸው ይህንን ሴራቸውን በማጋለጥ የበኩሏን እንደመትወጣም ተናግራለች።

አሸባሪውን ህወሓት እየተፋለመ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ደም መለገሷን አስታውሳ፣ አሁኑ ደግሞ  ለመደምሰስ መዘጋጀቷን ገልጻለች፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውደ በበኩላቸው "የምናደርገው ድጋፍ ለመከላከያ ሠራዊቱ የሞራል ስንቅ ሲሆን ለአሸባሪዎች ደግሞ ቅስም የሚሰብር ነው" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ በአገሩ ክብርና ሉዓላዊነት እንደማይደራደር አሸባሪው ህወሓት ይቅርና ውጭ ያሉ ጋላቢዎቹ ጭምር የሚያውቁት ሀቅ ነው፡፡

ህወሓት ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያ ክብሯንና ዝናዋን እንድታጣ ህዝቡም እንዲከፋፈል በርካታ ሴራዎችን መፈጸሙንም ተናግረዋል፡፡

በዜጎች ሁለንተናዊ ትብብር ከስልጣኑ እንደተወገደ ሁሉ ከምድረገጽ ለማጥፋት የዞኑ ህዝብ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን መሆኑን አስተዳዳሪው አስታውቀዋል፡፡

ህወሓትና ሽኔ አሸባሪዎች መሆናቸው በዜጎች ላይ እየፈጸሙት ያለው ግፍ ህያው ምስክር ነው" ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፣ የትኛውንም የአሸባሪውን ህወሓት ተላላኪ በማነፍነፍ ህዝቡ እንዲያጋልጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም