በወር አበባ ጊዜ ለሚኖር ህመም ሐኪም ማማከር ይገባል

1294

አዲስ አበባ ነሐሴ 14/2010 በወር አበባ ጊዜ ለሚያጋጥም ህመም ሀኪም ማማከር እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

ተፈጥሮ ለሴት ልጆች ከለገሰቻቸው ገፀ በረከቶች መካከል አንዱ የወር አበባ ነው ፡፡

የወር አበባ ከአስር ዓመት አንስቶ እስከ 45 አልፎ አልፎም እስከ 50 ዓመት ዕድሜ የሚዘልቅ ተፈጥሯዊ ዑደት ነው። ታዲያ በዚህ ተፈጥሯዊ ዑደት ወቅት ሁሉም ባይባልም አብዛኛው ሴቶች ይታመማሉ፡፡ ጥቂቶቹ ደግሞ በከባድ ሁኔታ ይሰቃያሉ፤ ህመሙንም መቆጣጠር አቅቷቸው እራሳቸውን እሰከመሳትም የሚደርሱ ሴቶች አሉ፡፡

የ22 አመቷ ብርቱካን ወልዴም ለረጅም ዓመታት “በወር አበባ ህመም ተሰቃይቻለሁ” ትላለች፡፡ ብርቱካን የህመሙንም ከባድነት እዲህ ታስረዳች፡፡

 በጣም ከባድ ነው ፡፡ ስራ ቦታም ሆነ ሌላ አካባቢ  ሊከሰት ይችላል፡፡ መምጫው አካባቢ ሲደርስ በጣም ነው የምጨናነቀው፤ ሰውነቴም ይቀንሳል፡፡ መቼ መጣ ፣ እንዴት መጣ ፣ያመኝ ይሆን? የሚለው ሁሌም ስለሚያሳስበኝ እፈራለሁ:: በጣም ነው የማስበው ያስጨንቀኛል፡፡

ብርቱካን ህመሙ ሲጀምራት ትኩስ ነገር በመውሰድ ለማስታገስ ትሞክራለች፡፡ ህመሙ ሲጸናባት ደግሞ ህክምና ትወስዳለች፡፡

በወር አበባ ወቅት ቁርጠት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ ፣የሆድና የወገብ ህመም፣ ማስታወክ እንዲሁም አለፍ ሲልም  እራስ መሳት ይከሰታል፡፡

ይህን መሰሉ ችግር የብርቱካን ብቻ ሳይሆን የብዙዎቹ ነውና ጉዳዩን ይዘን ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ስፕሻላይዝድ ሆስፒታል አምርተናል፡፡

የማህጸንና ጽንስ ህክምና ሀኪሙ ዶክተር ሙስጠፋ ነጋሽ የህመም ስሜቱ በተለያየ ምክንያት ለከሰት እንደሚችል አጫውተውናል፡፡

ከፋፍለን ስናየው መንስኤ የሌላቸው  እና ያላቸው ብለን እንከፍላለን። መንስኤ የሌለው የወር አበባ የሚባለው ብዙ ጊዜ ከእንቁላል መመረት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ነው፤ እንቁላል ሲመረት አብረው የሚለቀቁ ሆርሞኖች አሉ፡፡ በዚያም የተነሳ የማህፀን መኮማተር የሚያመጡ ሆርሞኖች አሉ።  መንስኤ ያላቸው ህመሞች ብዙ ጊዜ እድሜያቸው ገፋ ባሉ ሴቶች ላይ ነው የሚከሰተው።

ለዚህ መሰሉ ችግር መፍትሔው ማግባት ወይም የግብረ ስጋ ግንኙነት መፈጸም ተደርጎ ቢወድም ዶክተር ሙስጠፋ በሃሳቡ አይስማሙም፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከመውለድም ከግንኙነትም ጋር ምንም አይነት  ግንኙነት የለውም፤ ይሄ የወር አበባ ህመም አንዲት ሴት ብትወልድም  ከወንድ ጋር ብትገናኝም  ብታገባም ህመሙ ይቀጥላል፤ ይኖራል፡፡ አንድን ሰው ገፋፍቶ እንዲያገባ ወይም ደግሞ ወሲብ እንዲፈፅም ማድረግ ለዚህ ህመም መፍትሄ ሊሆን አይችልም። ማለት ይሄ በሳይንሳዊ መንገድ ያልተረጋገጠ ነው፡፡

የወር አበባ ህመም በሴት ልጅ ማህፀን ውስጥ የተፈጠረው እንቁላል ፈርሶ ሲወጣ የሚመጣ ህመም በመሆኑ አንድ ሴት በምታረግዝበት እዲሁም በምታጠባበት ወቅት  ይህ ተፈጥሯዊ ስርዓት ስለማይከናወን ህመሙ ላልተወሰነ ጊዜ ይጠፋል እንጂ ተመልሶ መምጣቱ አይቀርም ሲሉም ዶክተሩ አስረድተዋል፡፡

መንስኤ ያለው ህመም  የሚባለው ቀላል ቁርጠት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ ፣ቀላል የወገብ ህመም እና የመሳሰሉት ምልክቶች ሲኖሩት መንስኤ የሌለው የሚባለው ደግሞ ከባድ የሆድ እና የወገብ ህመም፣ ማስታወክ እንዲሁም አለፍ ሲል እራስ እስከመሳት የሚያደርስ ህመም ምልክቶቹ ናቸው፡፡

በሁለቱም ምክንያቶች ለሚከሰቱ ህመሞች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ በሙቅ ውሃ መታጠብ፣ የሞቀ ነገር ማህጸን አካባቢ ማስቀመጥ መፍትሔ መሆናቸውን ያብራሩት ዶክተር ሙስጠፋ ህመሙ የሚጸናባቸው ሴቶች ግን ህክምና ማግኘት እንዳለባቸው መክረዋል፡፡