ደቡብ ሱዳን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚደረግ የውጭ ጣልቃገብነትን አትደግፍም

77

ጥቅምት 27/2014 (ኢዜአ) ደቡብ ሱዳን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚደረግ የውጭ ጣልቃገብነትን እንደማትደግፍ በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን ተናገሩ።

ኢትዮጵያ ችግሮቿን በራሷ አቅም መፍታት የሚያስችል ልምድ ያካበተች አገር መሆኗንም አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ፒተር ሞርጋን ኢትዮጵያ በዓለም ታሪክ ውስጥ ቀደምት አገር መሆኗን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የ "ሊግ ኦፍ ኔሽን" እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራች መሆኗን ጠቅሰው፤ በዚህም የራሷን ችግር በራሷ አቅም እንዴት መፍታት እንዳለባት የካበተ ልምድ አዳብራለች ነው ያሉት፡፡

ደቡብ ሱዳንም ኢትዮጵያ ችግሮቿን በራሷ አቅም መፍታት እንደምትችል ጽኑ እምነት እንዳላት ገልጸዋል።

ይህ በመሆኑም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚደረግ የውጭ ጣልቃግብነትን ፈጽሞ አንደግፍም ብለዋል።

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት በቅርቡ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውን በማስታወስ "ኢትዮጵያ ሁሌም ከደቡብ ሱዳን ሕዝቦች ጎን ናት፤ ለእኛም ሁለተኛ አገራችን ናት" ብለዋል አምባሳደሩ፡፡

ኢትዮጵያ ቤታችን እንደሆነች ይሰማናል፤ በቤታችን ችግር ሲፈጠር ደግሞ ደስታችን ይርቃል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ረጅም ርቀት በጋራ ተጉዘዋል ያሉት አምባሳደሩ "በሁለት አገር የምንኖር አንድ ሕዝብ ነን" ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተያዘች ነጻ አፍሪካዊት አገር መሆኗን ያስታወሱት አምባሳደሩ፤ በዚህም የሁሉም አፍሪካዊያን ዓይን ኢትዮጵያ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ሠላም እንድትሆን ከመሻት ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ትምህርት በሚሆን መልኩ የተሳካ ሠላማዊ ምርጫ ማካሄዷንም አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ውህደት አይተኬ ሚና እንዳላት ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ሠላም ለቀጣናውም ፋይዳው የጎላ መሆኑን አውስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም