ለውጡን በተግባራዊ ስራ መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ ለሀገር አቀፉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ምስራቅ ሸዋ የተሰማሩ ወጣቶች ገለጹ

71
አዳማ  ነሀሴ 14/2010 የተጀመረው የለውጥ ጉዞ እውን እንዲሆን በተግባራዊ ስራ መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ ለሀገር አቀፉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ምስራቅ ሸዋ  አካባቢ  የተሰማሩ  ወጣቶች ገለጹ፡፡ በአካባቢው ከተሰማሩት መካከል ከደቡብ ህዝቦች ክልል ሸካ ዞን የመጣው ወጣት አስረሳሃኝ ደነቀ ለኢዜአ እንደገለጸው በሀገሪቱ  አሁን ላይ የህዝቦች መደማመጥ፣የጋራ ልምድና የባህል ለውውጥ መድረክ እየተፈጠረ ነው። " ወጣቱ ትውልድ የተሻለውን ጥበብ፣ እውቀትና አማራጮች ያስገኙልን ጠቅላይ ሚንስቴር ዶክተር አብይ አህመድን ለማጋዝ ያለብን የበጎ ተግባር ሥራ በዘላቂነት መስራት ሲንችል ነው" ብለዋል። አንዱ የሌላውን ባህል፣ታሪክና ወግ መማር እንዲችል ያሳያቸው ፕሮግራም ከመሆኑም ባለፈ ከዚህን በፍት ሰለኦሮሞ ህዝብ ምንነት ከሚሰማው በላይ ትልቅ እውቀትና ግንዛቤ ማግኘቱን ተናግሯል። ቆይታቸው ስለኦሮሚያ ብሎም ስለሀገራቸው ባህልና ታሪክ አውቀው የጋራ እሴቶችን  አጠናክረው ለማስቀጠል ስንቅ ያገኙበት መሆኑን የገለፀው ደግሞ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጣው ወጣት ሆኖክ ደረጀ ነው። በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች አሁን እየታዩ ያሉት አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን ለመታገልና የተጀመረውን  የለውጥ ጉዞን ለማሳካት ከመንግስት ጎን ሆነው እንደሚሰሩ ተናግረዋል። የሠላም፣የልማትና የለውጥ አምባሳደር ሆነ የህዝብ ለህዝብ ትስስርና  የሀገር አንድነትን ለማጠናከር የየአከባቢያቸውን ህብረተሰብ የማስገንዘብ ሥራን እንደሚያከናውኑ አመልክቷል የህዝቦች ሠላም፣ፍቅርና አንድነትን ለማረጋገጥ  የተጀመረውን ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ በተግባራዊ ስራ መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ ወጣቶቹ  ገልጸዋል፡፡ የምስራቅ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ታምራት በበኩላቸው "ሀገር አቀፉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ የህዝቦችን አብሮነት፣ፍቅርና አንድነትን የሚያጠናክሩ ተግባራት ነው "ብለዋል። ወጣቶቹ በቆይታቸው አዳማ ከተማን ጨምሮ በዞኑ በደም ልገሳ ፣ በከተሞች ፅዳት ፣በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ስራ፣ አረጋዊያን በማንከባከብ ፣ የጎልማሶችና የማጠናከሪያ ትምህርት ላይ በመሳተፍ ህዝባዊ ወገንተኝነት ማሳየታቸውን አመልክተዋል። " ለህብረተሰቡ ያሳዩት ፍቅርና ያከናወኑት ተግባር ታሪክ የማይረሰው ነው "ያሉት አቶ ጌታቸው ወጣቶቹ የኦሮሚያ ክልል የሠላምና የልማት አምባሳደር መሆናቸውንም ተናግረዋል። ወጣቶች ከሚኖሩበት አካባቢ በመውጣት እውቀትና ጉልበታቸውን ለበጎ ዓላማ ማዋላቸው ለሀገራዊ አንድነትና ለህዝቦች ትስስር መጠናከር ወሳኝ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የኦሮሚያና የኢትዮዽያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ወጣት ታሬቀኝ አብዱል ጀባር ነው፡፡ አሁን የተጀመረው አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ውጤታማ እንዲሆንና ሀገሪቱ ወደ ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ መስመር እንዲትገባ መስራት የወጣቶች የቀጣይ ጊዜ ሥራ መሆኑንም አመልክቷል። " የተቀናጀ የበጎ አድራጎት ሥራ ለሀገራችን ሠላም " በሚል መሪ ሀሳብ  በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማና ምስራቅ ሸዋ ዞን የተሰማሩ ወጣቶች በአካባቢው የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው  ትናንት አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል፡፡ የእውቅና የምስክር ወረቀትና  ልዩ ልዩ የኦሮሞ የባህል አልባሳት ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም